በሊቢያ አፍሪካውያን ስደተኞች ለባሪያ ንግድ የጨረታ ሽያጭ ይቀርባሉ ተባለ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 5/2010)በሊቢያ አፍሪካውያን ስደተኞች ለባሪያ ንግድ የጨረታ ሽያጭ እንደሚቀርቡ የሚያሳይ በምስል የተደገፈ መረጃ ይፋ ሆነ።

ሲ ኤን ኤን ይፋ ባደረገው በዚህ መረጃ ከ10 በላይ የሚሆኑና ከኒጀር የመጡ ስደተኞች በ6 ደቂቃ ውስጥ በጨረታ መሸጣቸውን አጋልጧል።

ይህ ክስተት ከዘመናት በፊት የተሻረውን የሰው ልጅን እንደሸቀጥ የመሸጥ አስከፊነት እንደገና እንዲታወስ አድርጓል ሲል ዘገባው አመልክቷል።

በሊቢያ የሚገኙ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ከተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የሚሄዱ ስደተኞችን በጨረታ እንደሚሸጧቸው ሲ ኤን ኤን በምስል አስደግፎ ያወጣው መረጃ አጋልጧል።

ሲ ኤን ኤን በቅድሚያ የተላከለትንና ከምዕራብ አፍሪካ የመጡ ስደተኞች በጨረታ ሲሸጡ የሚያሳየውን ምስል መሰረት አድርጎ የራሱን ጋዜጠኞችና የምስል ባለሙያዎች በመላክ የባሪያ ንግዱ በጨረታ ሲከናወን የሚያሳየው ሪፖርት ከረጅም አመታት በፊት የተሻረውን የባሪያ ንግድ አስከፊ ገጽታ እንደገና እንዲታወስ አድርጓል።

“ትልቅ ጠንካራ ልጆች ለግብርና ስራ” ይላል ፊቱን የሸፈነው አጫራቹ ተጫራቾችም እጃቸውን እያወጡ “400,500,800 ፓውንድ” እያሉ ንግዱን ሲያጧጡፉ ያሳያል ሲ ኤን ኤን በምስል አስደግፎ ይፋ ያደረገው መረጃ።

ወደ አውሮፓ ለመሻገር ተስፋን ሰንቀው በሊቢያ በርሃ ላይ ጉዟቸውን የጀመሩ ከኒጀር፣ማሊ፣ናይጄሪያና ጋና የሄዱ ስደተኞች ከሊቢያ መዲና ትሪፖሊ ወጣ ብላ በምትገኝ ከተማ በአማካኝ በ400 ዶላር በጨረታ ሲሸጡ ተስተውሏል።

በዚህ ሲ ኤን ኤን በለቀቀው ምስል ውስጥ ከ10 በላይ የሚሆኑና ከኒጀር የመጡ ስደተኞች በ6 ደቂቃ ውስጥ በጨረታ ተሽጠዋል።

በወር ሁለት ጊዜ ለሚካሄደው ለዚሁ ጨረታ የሚመረጡት ስደተኞች እንደ እድለኛ ነው የሚቆጠሩት።

አጫራቾቹም ስደተኞቹን “ባዳዬ” ብለው ይጠሯቸዋል።”ሸቀጥ” እንደማለት ነው በአረብኛ።

“ወደ ሀገራችን ይውሰዱን እዚህም የመጣነው ተሽጠን ነው።” “ተመልከቺ የገላዬን ጠባሳ የተደበደብኩት ነው” ያላሉ አንዳንዶቹ ለሲ ኤን ኤን ጋዜጠኛ ኒማ ኤልባገር።

ብዙዎቹ ጓደኞቻቸው በየመንገዱ እንደሞቱም ስደተኞቹ ተናግረዋል።

ከጨረታው በኋላ የሲ ኤን ኤን ጋዜጠኛ ለማናገር የሞከረቻቸው ሁለት ለጨረታ የቀረቡ ስደተኞች በሆነው ነገር እጅግ ከመደናገጣቸውና ሁሉንም ሰው ማመን ካለመቻላቸው ጋር ተያይዞ ምንም አይነት ቃል መናገር አልቻሉም።

ሲ ኤን ኤን ጨረታውን የሚያሳየውን ምስል ለሊቢያ ባለስልጣናት ማሳየቱንና ባለስልጣናቱም ምርመራ እንደሚያካሂዱ ተናግረዋል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን በየአመቱ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሊቢያን ድንበር አቋርጠው ይገባሉ።

ብዙዎቹ ያሰቡበት ሳይደርሱ ግን መንገድ ላይ ይቀራሉ።–ተረፉ የተባሉትም ለባሪያ ንግድ ተጋልጠዋል።

በሚያዚያ 2008 30 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በአይሲስ አሸባሪ ቡድን አሰቃቂ በሚባል ሁኔታ መገደላቸው አይዘነጋም።

መስቀልና ሌሎች ክርስትናን የሚያመላክቱ ነገሮችን በመያዛቸው ከፊሎቹ በቢላ ሲታረዱ ሌሎቹ ደግሞ በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ የሚያሳየው ምስል አሁንም ከኢትዮጵያውያን ሕሊና አልጠፋም።

በጨረታ የተሸጡት እነዚህ አፍሪካውያንም ከዘመናት በፊት የተሻረውን የሰው ልጅን እንደሸቀጥ መሸጥ አስከፊነት እንደገና እንዲታወስ አድርጓል።