በአዶላ ክብረመንግስት የተቃውሞ ሰልፍ ተካሄደ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 6/2010) በአዶላ ክብረመንግስት ዛሬ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሄደ።

ተቃውሞው የወያኔ አገዛዝ በቃን በሚል የተካሄደ ሲሆን ሰሞኑን በሶማሌ ክልል አጎራባች አካባቢዎች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ህዝቡ በቁጣ አደባባይ መውጣቱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በቡሌ ሆራ ሀገረማርያም ዩኒቨርሲቲም ተማሪዎች ተቃውሞ ማድረጋቸው ታውቋል።

በመቱ ዩኒቨርስቲ የጸጥያ ሃይሎች ከተማሪዎች ጋር መጋጨታቸውም ተገልጿል።

በባሌ ሮቤም በቄሮዎች ከፍተኛ ተቃውሞ መካሄዱን ለማወቅ ተችሏል።

ዛሬ አዶላ ክብረመንግስት ከ10ሺህ በላይ ህዝብ የተካፈለበት የተቃውሞ ሰልፍ የተካሄደው ሰሞኑን በጉጂ ዞን የተከሰተው ግጭት የ10ሰዎችን ህይወት ማጥፋቱን ተከትሎ ነው።

ኢሳት ያነጋገራቸው የአዶላ ነዋሪዎች እንደገለጹት በሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል የሚፈጸመው ጥቃት መቆም ባለመቻሉ ነዋሪው ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ወድቋል።

ይህን ስጋት ለማሳየትና በህወሀት መንግስት ላይ ተቃውሞ ለማሰማት ነበር ዛሬ የተቃውሞ ሰልፍ የተደረገው።

ህዝቡ በተለይ መከላከያ ሰራዊቱን በተመለከተ ጠንካራ ተቃውሞ አሰምቷል። ግጭቱን ማብረድ እየቻለ ምንም ዓይነት ርምጃ አለመውሰዱ ነዋሪውን አስቆጥቷል።

ከአዶላ ክብረመንግስት የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ የጀመረው ተቃውሞ መላውን የከተማዋ ነዋሪን በማካተት የተካሄደ ሲሆን የህወሀት መንግስት አገዛዝ እንዲያበቃ ተጠይቋል።

ጋብ ብሎ የነበረውና በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በድጋሚ መቀስቀሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና ህዝቡ ቀዬ መንደሩን ትቶ በመሰደድ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል በቡሌ ሆራ ሀገርማርያም ዩኒቨርስቲ ተቃውሞ መቀስቀሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በዩኒቨርስቲው የተነሳውን ተቃውሞ ለማስቆም የጸጥታ ሃይሎች የወስዱት ርምጃ ግጭትን በመፍጠሩ በርካታ ተማሪዎች መጎዳታቸው ታውቋል።

በኢሉባቡር መቱ ዩኒቨርሲቲም የመማር ማስተማሩ ሂደት እስካሁን ያልተጀመረ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ግቢውን ለቀው መውጣታቸውን የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በባሌ ሮቤ ከተማ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲካሄድ መዋሉን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የከተማዋ ቄሮዎች ባስተባበሩት በዚሁ ተቃውሞ ላይ የህወሀት መንግስት በአስቸኳይ ስልጣን እንዲለቅ ተጠይቋል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ይፋ የተደረገው የ1 ዓመት የብሄራዊ ደህንነት ዕቅድ ተግባራዊ መሆን በጀመረ ማግስት ህዝባዊ ተቃውሞ ተጠናክሮ መቀጠሉ ህዝቡ ለየትኛውም አዋጅና መመሪያ ተገዢ እንደማይሆን ያረጋገጠበት ነው ሲሉ የፖለቲካ ታዛቢዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።