እነ ንግስት ይርጋ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተባሉ

(ኢሳት ዜና–ህዳር 5/2010)በጎንደሩ ሕዝባዊ ተቃውሞ በሽብር የተከሰሱት እነ ንግስት ይርጋ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተባሉ።

እነ ንግስት ይርጋ ያቀረቡት መቃወሚያ ግምት ውስጥ ሳይገባ እንዲከላከሉ የአገዛዙ ፍርድ ቤት ወስኖባቸዋል።

ፍርድቤቱ እነ ንግስት ይርጋን ጥፋተኛ ያላቸው የሰላማዊ ተቃውሞ መገለጫ በሆኑ የሰልፍ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ነው።

በእነ ንግስት ይርጋ መዝገብ በጎንደሩ ሕዝባዊ ተቃውሞ በጸረ ሽብር ሕጉ የተከሰሱት የሰላማዊ ተቃውሞ አንቀሳቃሾች እንደ ማስረጃ የቀረበባቸው በደህንነት መስሪያ ቤቱ የቀረቡ ጉዳዮች ናቸው።

በተለይም በወጣቷ ንግስት ይርጋ ላይ ከቀረቡት ጉዳዮች መካከል በጎንደሩ ሰልፍ የለበሰችውን ልብስ አውልቃ ከ5 ሺ ብር በላይ ሰብስባለች፣የኮለኔል ደመቀ ዘውዱን ፎቶ ባነር አሰርታለች።

ፎቶግራፉ ያለበትን ቲሸርትም በ120 ብር ገዝታለች በሚል ነው።

በሰልፉ ላይም እቴጌ ጣይቱ ተብላ ተጠርታለች የሚል እንዳለበትም ነው የተገለጸው።

ከተከሳሾችም መካከል 4ኛ ተከሳሽ አወቀ አባተ የአባልነት ፎርም ሞልቷል ሲባል 5ኛ ተከሳሽ በላይነህ አለምነህ ደግሞ ቀይ ካርድ ይዛችሁ አደባባይ ውጡ ብሏል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

እነዚህ ሁሉ የሰላማዊ ተቃውሞ መገለጫዎች ቢሆኑም እዚህ ላይ ግን በሽብር የሚያስከስሱ ሆነዋል።

አቃቢህግ ባቀረበው የሰነድ ማስረጃ እነ ንግስት ይርጋ ያቀረቡት መቃወሚያ ተቀባይነት አላገኘም።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የጥፋተኝነት ውሳኔ ሲሰጥም መቃወሚያውን ግምት ውስጥ ሳያስገባ መሆኑ ታውቋል።

እናም ውሳኔው የጥፋተኝነት በመሆኑ እነ ንግስት ይርጋ የመከላከያ ምስክራቸውን ለታህሳስ 12ና 13 እንዲያቀርቡ ታዘዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም አቶ ማሙሸት አማረ ለቀረበበት የሰነድ ማስረጃ ምላሹን እንዲሰጥ ለሕዳር 11 መቀጠሩን ለማወቅ ተችሏል።