በለንደን እየተካሄ ባለው 17ኛው ኦሎምፒክ ውድድር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ 10፣000 ሜትር በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ አጠለቀች

ሐምሌ ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ውድድሩ ከመካሄዱ በፊት ኬንያውያን ወርቁ የእነሱ እንደሆነ ደምድመው  ለተለያዩ ሚዲያዎች ብዙ ብለዋል።

በተለይ በዳጉ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ 5 000 እና በ 10 000 የድርብ ወርቅ ሜዳል ባለቤት የሆነችውና በትናንት ምሽቱ የ 10000 ሜትር ውድድር ሦስተኛ የወጣችው ቪቪያን  ቸሩዮት ወድድሩ ከመካሄዱ በፊት፤ ወርቁ የእሷ እንደሆነ  በእርግጠኝነት በማወጅ፦”ኬንያውያን ከአሁን ጀምረው መጨፈር ይችላሉ” ነበር ያለችው።

የኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሊቀ-መንበር  እና የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት ኢሳያስ ኪፕላጋት በበኩላቸው፦” ቪቪያን በዚህ የውድድር ወቅት  ከሚገባው በላይ ተዘጋጅታለች። ጥሩ ሠርታለች።የወርቅ ሜዳሊያ እንደምታገኝ እርግጠኛ ነኝ” ነበር ያሉት።

ኪፕላጋት በዚህ ሳይወሰኑ  የ 10 ሺህ ሜትር ውድድሩ እንዳለቀ፤ ቪቪያን የወርቅ ሜዳሊያ ለመቀበል በሚወጣበት መድረክ ላይ እንደሚያዩዋት፤አለያም ወደ መድረኩ ራሳቸው ይዘዋት እንደሚሄዱ ነበር በተስፋ የገለጹት።

“አንችስ ምን ትያለሽ?” ተብላ የተጠየቀችው ጥሩነሽ ዲባባ ግን፦” አሁን ምንም አልልም።ሜዳው ላይ ስንገናኝ፤አሸናፊው ይለያል” ነበር ያለችው።  ውድድሩም ተጀመረ።

ጃፓናውያኖቹ ሂቶሚ ኒያ ፣ ካዮኩ ፉኩሽ  እና  ሚካ ዮሺካዋ ተስፈንጥረው   በመውጣት ሩጫውን መምራት ጀመሩ።

ቀሪዎቹ  ወደ 20 የሚሆኑ  አትሌቶች ጃፓናውያኑን  በቅርብ ርቀት በመቆጣጠር እጅብ ብለው መሮጣቸውን ቀጠሉ።

የጃፓናውያኑ መምራትም ሆነ እጅብ ብሎ የመሮጡ ትዕይንት ግን፤ ከ 14ኛው ደቂቃ በሁዋላ አልቀጠለም።

ሰባት ባቡሮች ፍጥነታቸውን  ጨመሩ። ሦስት ኢትዮጵያውያን፣ ሦስት ኬንያውያን እና አንድ ትውልደ-ኢትዮጵያዊት ባህሬናውያን።

ከበርካታ አገሮች የተውጣጡ  22 አትሌቶች የተሳተፉበት ይህ ውድድር፤ በተለይ ከ 20ኛው ደቂቃ በሁዋላ  በሁለት አገሮች መካከል የሚካሄድ መሰለ-በኢትዮጵያውያን እና በኬንያውያን።

በእርግጥም ኢትዮጵያ ውርቅ እንድታገኝ ከተፈለገ  እርስ በርስ እየተፈራረቁ እስከዚህ ደቂቃ የደረሱት የሁለቱ አገሮች ሯጮች በዚህ መልኩ መቀጠል የለባቸውም።ማጠናቀቂያ መስመር ላይ በፍጥነት የመወንጨፍ ችሎታ ያላቸው ቅልጥመ-ረዣዥሞቹ ኬንያውያን ከወዲሁ መዳከም ይኖርባቸዋል።

በትናንት ምሽቱ ውድድር ወርቅነሽ ኬዳኔ ይህን ሀላፊነት በልዩ ብቃት ተወጥታለች።

ውድድሩ ገና ከሰባት ዙር በላይ እየቀረው ወርቅነሽ ባለ በሌለ ሀይሏ ኬንያውያኑን ወደፊት ይዛ ስትወጣ፤ጥሩነሽ ከሁዋላ እግር እግራቸውን መከተል ቀጠለች።

የመጨረሻው ዙር ሲቀርም፤   ኢትዮጵያዊቷ ተወርዋሪ ኮከብ ማርሿን ቀይራ እንደ ሮኬት  ተወነጨፈች። ኮሜንታተሮች    በእርግጠኝነት መንፈስ፦“ ኢትዮጵያ ዲባባ…ኢትዮጵያ ዲባባ…ማለት ቀጠሉ። ውድድሩ ሊጠናቀቅ 200 ሜትር ሲቀር ጠይሟ ወጣት ይበልጥ  ተምዘገዘገች። ዋነኛ ተቀናቃኞቿን  በረዥም ርቀት በማስከተልም- የውድድሩን ገመድ በጠሰች።

የፎከሩባትን ኬንያውያን በቃል ሳይሆን በተግባር አናገረቻቸው።

ጥሩነሽ ዲባባ ርቀቱን በ 30 ደቂቃ ከ 26ነጥብ 37 ሰከንድ በ አንደኝነት በማጠናቀቅ  በለንደን ኦሎምፒክ ለራሷና ለሀገሯ  የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አሰገኝታለች። ኬኒያዊያኖቹ ሳሊ ኪፒጎ እና  ቪቪያን ቼሩዮት ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን የብርና የነሀስ ሜዳሊያ አግኝተዋል።

ከኬንያኖቹ አትሌቶች ጋር አንገት ላንገት ተናንቃ  እንዲዳከሙ በማድረግ፤ ኢትዮጵያ ላገኘችው ድል ከፍተኛ ተጋድሎ ስታደርግ ያመሸችው ጀግናዋ ወርቅነሽ ኪዳኔ በ 30 ደቂቃ ከ 39 ነጥብ 38 ሰከንድ በአራተኛነት፤ ለባህሬን የሮጠችው ትውልደ-ኢትዮጵያዊቷ በላይነሽ ኦልጅራ  በአምስተኛነት፤ ጅማሬዋ አስደሳች የነበረውና  በአጨራረስ በኩል ጥቂት የቴክኒክ ድጋፍ ብቻ  የሚያስፈልጋት ተሰፋ ሰጪዋ አትሌት ሽታዬ እሸቴ  በስድስተኛነት ውድድራቸውን ሲያጠናቅቁ፤ አዘጋጇ እንግሊዝ ያሰለፈቻቸው ዮሀን ፓቬይ እና ጁሊያ ብሌስዳሌ ሰባተኛና ስምንተኛ ወጥተዋል።

ከጅማሬው እጅብ ብለው ተስፈንጥረው በመውጣት ውድድሩን እስከ 13ኛው ደቂቃ ድረስ ሲመሩ ከነበሩት ሦስት ጃፓናውያን መካከል ሂቶሚ ኒያ እና ካዮኩ ፉኩሽ 9ኛ እና 10 ኛ ሲወጡ ሚካ ዮሺካዋ ደግሞ  በ 16 ኛ ደረጃ አጠናቃለች።

ቀደም ሲል በሁለት ዙር በተካሄደ የወንዶች 1500 ማጣሪያ ኢትዮጵያ ሦስት አትሌቶችን አሰልፋ ነበር። መኮንን ገብረመድህን ከመጀመሪያው ምድብ ሁለተኛ በመውጣት ማጣሪያውን ሲያልፍ፤ ከሁለተኛው ምድብ ተሾመ ድሪርሳ ፣ከሦስተኛው ምድብ ደግሞ አማን ወልዴ በተመሣሳይ ከመጨረሻ ሦስተኛ ሆነው በማጠናቀቅ ማጣሪያውን ሳያልፉ ቀርተዋል።

ይህ ዜና እሰከሚጠናቀርበት ጊዜ ድረስ በሴቶች 10፣000 ሜትር የተገኘው የወርቅ ሜዳሊያ ኢትዮጵያን ከ ዓለም በ 24 ኛ ፤ ከ አፍሪካ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።

ሶስት ወርቅ እና አንድ ብር ያገኘችው ደቡድ አፍሪካ ከ ዓለም በ 11ኛነት፤ከ አፍሪካ ደግሞ በአንደኝነት እየመራች ስትሆን ኬንያ ደግሞ በ አንድ ብር እና በ አንድ ነሀስ በ 35 ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ኢትዮጵያ፤በቀጣይ በሚደረጉ የረዥም ርቀት ሩጫ ውድድሮች ተጨማሪ ሜዳሊያዎች  በማግኘት ከፍተኛ የደረጃ ማሻሻል ታሳያለች ተብሎ ይጠበቃል።

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide