በሀገሪቱ ለተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ የግብጽና የኤርትራ መንግስትን ተጠያቂ ተደረጉ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 4/2010) የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ለተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ የግብጽና የኤርትራ መንግስትን ተጠያቂ አደረገ።

በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ በነበረው ግጭት የጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሙን መንግስት ገልጿል።

“ወቅታዊ የሀገራችንን ሁኔታ ትንታኔ መሰረት ያደረገ እቅድ” በሚል ርዕስ በጥቅምት 2010 የወጣውና ለጸጥታና ደህንነት ምክር ቤት የቀረበው ሪፖርት የሀገሪቷን የጸጥታ ሁኔታ ይገመግማል።

አዲስ ስታንዳርድ በድረገጹ “ሾልኮ የወጣ” በሚል ባቀረበው ባለ 26 ገጽ ሪፖርት የፌደራል ስርአቱን የሚፈታተኑ ክስተቶች ማጋጠማቸው፣በየጊዜው በሚከሰቱ ግጭቶች በርካታ ሰብአዊና የንብረት ጉዳት ማድረሳቸው፣ግጭቶቹ ሀገራዊና አካባቢያዊ መልክ መያዛቸውን ይዘረዝራል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የሀገሪቱ ገጽታ እየተበላሸ መሄዱንና ኢኮኖሚዋም በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳቱን ይገልጻል።

የእቅዱ መነሻ ውስጣዊ ሁኔታ የሚያሳይበት ክፍል ጸረ ሕዝብ ሃይሎች በግብጽና ኤርትራ መንግስታት አዝማችነትና የቅርብ ድጋፍ ተጠቅመው ስልታዊ የጋራ ግንባር በመፍጠር ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሁከት፣በብጥብጥና በአመጽ ለማፍረስ እየተረባረቡ መሆናቸውን ይገልጻል።

ለዚህ ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው ደግሞ በውስጣችን የተከሰተው ተጋላጭነት ነው በማለት ያስገነዝባል።

በየጊዜው በሚከሰቱ ግጭቶች በርካታ ሰብአዊና የንብረት ጉዳት ደርሷል የሚለው የመንግስት ሪፖርት በተለይም በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የነበረው ግጭት ሰፊ ጉዳት ማድረሱን ይናገራል።

 

ከደረሱት ጉዳቶች መካከል ሰፊው ሕዝብ ከቀዬው መፈናቀሉ፣የጅምላ ጭፍጨፋ(ጂኖሳይድ) መካሄዱ፣ኢሰብአዊና አሰቃቂ ግድያዎች መፈጸማቸውና የሕዝብ የመኖርና የመንቀሳቀስ መብት ስጋት ውስጥ የወደቀበት ነው ሲል በማሳያነት ያነሳል።

በህዝቦች ስነልቦና ላይ ጠባሳ የፈጠረ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ስም የሌለውና ሀላፊነት በግልጽ የማይወስድ ሽብርተኝነት እየተስፋፋ እንዳለ ማየት ተችሏል በማለትም ያክላል።

ከተፈጠረው ችግር ጋርም በተያያዘ ኢኮኖሚው በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዳ መሆኑን ሪፖርቱ ይገልጻል።

ሪፖርቱ ሲቀጥልም ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር መስፋፋት፣መሰረታዊ ሸቀጦችን መደበቅና እጥረት መፍጠር ብሎም የውጭ ምንዛሪን መሸሸግና ማሸሽ እየታዩ ያሉ ክስትቶች መሆናቸውን አስቀምጧል።

አንዳንድ ባለሃብቶችና ኢንቬስተሮች ገንዘባቸውን ወደ ውጭ እያሸሹ መሆናቸውን የሚያሳዩ ጥቆማዎች እየወጡ መሆናቸውንም ሪፖርቱ አምልክቷል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የውጭም ሆነ የውስጥ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተዳክሟል።

የጎብኝዎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።–በሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት ይገኙ የነበሩ እርዳታዎችም ጥርጣሬ ውስጥ ገብተዋል ይላል ሪፖርቱ።

የህግ የበላይነት እየተከበረ አይደለም ሲል የሚገልጸው ሪፖርቱ በነዚህ ሁለትና ሶስት አመታት ብቻ በርካታ የህግ ጥሰቶችና ጸረ ህዝብ ድርጊቶች ተፈጽመዋል ብሏል።

በተለይም እንደ አርበኞች ግንቦት 7 እና ኦነግ የመሳሰሉ ድርጅቶች እንደፈለጉ የሚፈነጩበትና በህግ የሚጠየቁበት ሁኔታ አለመፈጠሩን ይናገራል ሪፖርቱ።

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ስጋት ውስጥ መግባቱንና ችግሮቹ እንደማይፈቱ ተስፋ የቆረጠበትና ዋስትና ያጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ከፍተና የሆነ የፕሮፓጋንዳ ጦርነት እየተካሄደብን ነው በማለት የሚገልጸው ይህ የመንግስት ሪፖርት ጸረ ሕዝብ ሃይሎች ያላቸው አካላት ከፍተኛ መሳሪያና ተተኳሽ ግዥና ፍለጋ ላይ መሆናቸውን ይናገራል።

ከፍተኛ ገንዘብ ለጦርነት እያሰባሰቡ መሆኑን እንዲሁም በርካታ ሃይሎችን በዙሪያቸው እያደራጁ ነው ሲል ያክላል።