የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ እንደገና ማገርሸቱ ተሰማ

(ኢሳት ዜና–ህዳር 1/2010)የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ እንደገና ማገርሸቱ ተሰማ።

ቀውሱ እንደገና ያገረሸው ባለፈው ቅዳሜ የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣኔን ለቅቄያለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት ሁቲዎች ባለፈው ቅዳሜ ወደ ሳውዲ ያስወነጨፉት የረጅም ርቀት ሚሳኤል ጉዳይም ሌላኛው የውጥረቱ ምክንያት ሆኗል።

የሳውዲ ዜግነትን ደርበው የያዙት የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳአድ ሐሪሪ ባለፈው ቅዳሜ ከሳውዲ ሪያድ ሆነው የግድያ ሙከራ ሊደረግብኝ እየተጠነሰሰ ነው በሚል ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ካሳወቁ በኋላ ሌባኖስን ትልቅ ቀውስ ውስጥ ከቷታል።

ሐሪሪ የግድያ ሙከራው በማን ሊደረግ እንደታቀደ በግልጽ ባያስቀምጡም ኢራን በሀገራቸውም ሆነ በአካባቢው አረብ ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷን አውግዘዋል።

የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሳውዲ ሆነው ከስልጣን መልቀቃቸውን ባሳወቁበት በዛው እለት የሳውዲው አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን በዝርፊያ ጠርጥሬያቸዋልሁ ያሏቸውን የሳውዲ ልኡላንና ሚኒስትሮችን እንዲሁም ነጋዴዎችን ጠራርገው በቁጥጥር ስር ማዋላቸው የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከስልጣን የመልቀቅን ወሬ ጆሮ ዳባ ልበስ እንዲባል አድርጎት ነበር።

ከተያዙት ውስጥም በኢትዮጵያ ንግድና ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ የያዙት መሐመድ አላሙዲ እንደሚገኙበትም ይታወቃል።

በአብዛኛው የሱኒ እምነት አራማጅ የሆነችው ሳውዲ አረቢያ የሺአ እምነት አራማጅ ከሆነችው ኢራን ጋር ለዘመናት የቆየ ቁርሾ እንዳላት ይታወቃል።

ይህን ቁርሾ ተከትሎም በየመን ስልጣኑን የተቆጣጠሩትና በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት ሁቲዎች ባለፈው ቅዳሜ ወደ ሳውዲ አይሮፕላን ማረፊያ ያስወነጨፉት የረጅም ርቀት ሚሳኤል በሳውዲ ጸረ ሚሳኤል መሳሪያዎች ኢላማውን ሳይመታ እንዲከሽፍ ሆኗል።

ሳውዲ አረቢያ ድርጊቱ በኢራን እንደተፈጸመ እርግጠኛ ነኝ ለዚህ ደግሞ በእጄ የገቡት የሚሳኤሉ ፍርስራሾ ማስረጃዬ ናቸው ብላለች።

የሳውዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አል ጆቢር ለሲ ኤን ኤን ኢራን በሳውዲ ላይ ጦርነት ከፍታለች በየመን ያሉ ሁቲዎችንም ታስታጥቃለች ሲሉ ከሰዋል።

የሊባኖስ መንግስት ባለስልጣናት የሱኒ እምነት ተከታይ የሆኑትንና በሳውዲ የሚደገፉትን ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን የሳውዲ መንግስት የቁም እስረኛ አድርጓቸዋል ሲሉ አቤቱታቸውን በማሰማት ላይ ናቸው።

የሚፈልጉትንም እንዳይናገሩ በሳውዲ ተጽእኖ ስር ወድቀዋል ይላሉ።

የሊባኖሱ ፕሬዝዳንት ሚቼል ኦዎን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አድርገዋል።

የስልጣን መልቀቂያውንም ቢሆን ወደ ሀገራቸው ካልተመለሱ አልቀበለውም ብለዋል።

ይህም በአብዛኛው የሱኒ እምነት አራማጇ ሳውዲ ከሺአ እምነት ተከታዮቹ ሊባኖስና ኢራን ጋር ውጥረት በመስፈኑ ወደ ጦርነት እንዳያመራ ስጋትን ጭሯል።

በዚህ መሀልም በሊባኖስ የፖለቲካና ወታደራዊ ተጽእኖ ፈጥሪ የሆነው ሂዝቦላ ሳውዳረቢያ በሊባኖስ ጉዳይ ጣልቃ ገብታለች ሲል ይከሳል።

በመካከላኛው ምስራቅ የኢራን ሃያልነት የሚያሰጋት ሳውዲ የኢራን ጉዳይ እኩል የሚያሳስባት እስራኤልን ከጎኗ ስታሰልፍ ኢራን በበኩሏ የሊባኖሱን ሂዝቦላንና በየመን ያሉ ሁቲዎችን በመጠቀም የእጅ አዙት ግጭት ውስጥ ገብታለች።