በመቱ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እስካሁን አለመረጋጋታቸው ተነገረ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 4/2010)በመቱ ዩኒቨርስቲ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ተማሪዎች እስካሁን አለመረጋጋታቸው ተነገረ።

በተማሪዎችና በአስተዳደሩ እንዲሁም እርስ በርስ የተከሰተው ግጭት ከፍተኛ ስጋት በመፍጠሩ ከግቢው የወጡ ተማሪዎች እስካሁን አልተመለሱም።

የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ከዩኒቨርስቲው አመራሮች ጋር ሁኔታውን ለማረጋጋት ቢሞክሩም የኦሮሚያ፣የአማራና የትግራይ ተማሪዎች በስጋት ምክንያት ግቢውን ለቀው ወጥተዋል።

በኦሮሚያ ነገሌ ቦረናና በጅጅጋ ድንበር አካባቢም ግጭቱ ማገርሸቱ ተነግሯል።

በመቱ ዩኒቨርስቲ ለግጭት መንስኤ የሆነው በተማሪዎች መካከል ብሄርን መሰረት ያደረገ ክፍፍል ነው።

በዩኒቨርስቲው ግጭት ሲነሳ በስጋት ምክንያት ዩኒቨርስቲውን ሊቀው የወጡ የትግራይ ተወላጆች ወደ ጋምቤላ ሸሽተው ቆይተው ነበር።

በጋምቤላ ባሉ የትግራይ ተወላጆችና በክልሉ አስተዳደር እንክብካቤ የተደረገላቸው ተማሪዎቹ ሁኔታው ተረጋግቷል በሚል ወደ ግቢያቸው ቢመለሱም ሁኔታው ተባብሶ ነው የጠበቃቸው።

በኦሮሞና የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች መካከል ግጭት ባይኖርም በኋላ ላይ ግን አንድ የአማራ ተማሪ ላይ ድብደባ በመድረሱ ሁለቱን ለማጋጨት የአገዛዙ ሴራ እንዳለበት አመላክቷል ተብሏል።

በመቱ ዩኒቨርስቲ የተጀመረውን ግጭት በመስጋት የግቢው ተማሪዎች በየቤተክርስቲያኑና በየመስጊዱ ውስጥ መጠለላቸው ተነግሯል።

በመቱ ዩኒቨርስቲ ያለውን ችግር መነሻ በማድረግ ከትምህርት ሚኒስቴር የተወከሉ የስራ ሃላፊዎችና ከኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የተወከሉበት ቡድን ተማሪዎችን ለማነጋገር ሞክሯል።

በውይይቱ ወቅትም የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ተነስተው ምክትል ፕሬዝዳንቱ እንዲሾሙ ጠይቀዋል ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በጅጅጋ ድንበር አቅራቢያ በኦሮሚያ ክልል ሁለት ሰዎች ተገድለው ተገኝተዋል።

በዚሁ ክልል ነገሌ ቦረና ደግሞ 6 ሰዎች መገደላቸው ነው የተነገረው።

በኦሮሚያ ያለው ግጭት እንደገና እያገረሸ መሆኑ ይነገራል።ይህ ግጭት ደግሞ እየተባባሰ የመጣው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና የኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ብቻ ናት ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

ይህን ማለታቸው ደግሞ ግጭት እንደገና በብሔሮች መካከል እንዲቀስቀስ ሕወሃት በእሳቸው በኩል መልዕክት እያስተላለፈ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።