መጋቢት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሀረር ከተከሰተው የእሳት አደጋ ጋር በተያያዘ ታስረው ከነበሩት ሰዎች መከካል አንዳንዶች ተለቀዋል።
ፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቁ ውሳኔ ካስተላለፈባቸው 7 ሰዎች መካከል ለአሜሪካ ድምጽ ቃለምልልስ ሰጥተዋል ተብለው የታሰሩት አቶ ገብረመድህን ገብረ መስቀል እንዲሁም 4ቱ የመብራት ሀይል ሰራተኞችም ተለቀዋል።
ይሁን እንጅ በሀረሪ የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኛ የነበረው ጋዜጠኛ ጀማል ዳውድ አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኝና ጉዳዩን ከሽብርተኝነት ጋር በማያያዝ ለመክሰስ መታሰቡን ለማወቅ ተችሎአል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የንግድ ቢሮ ድርጅታቸው የተቃጠለባቸውን ነጋዴዎች ጠርቶ የተሰበሰበውን 15 ሚሊዮን ብር ስለማከፋፈል አወያይቶ ነበር። ነጋዴዎች በበኩላቸው 15 ሚሊየን ብር ለ1 ሺ ተጎጂዎች ሲከፋፈል የሚደርሰን 15 ሺ ብር ነው፣ ብሩም በአሁኑ የኑሮ ውድነትና ብር በወደቀበት ወቅት ሁለት ካርቶን እቃ እንኳ የማይገዛ በመሆኑ ገንዘብ ይጨመርልን ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
ከመንግስት ባለስልጣናት በኩል ግን ይህ ነው የሚባል በቂ መልስ ሳያገኙ ቀርተዋል። የተለያዩ የሃይማኖት ተቋሟት እርዳታ ለመለገስ ቢያስቡም፣ የመንግስት ባለስልጣናት መንግስት በከፈተው አካውንት ካልሆነ በቀጥታ ለተጎጂዎች በሚደርስ አካውንት መግባት የለበትም በሚል በማስጠንቀቁ ችግር መፈጠሩ ታውቋል።