መጋቢት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የቀበሌ 10 ነዋሪ የሆነው ዳንኤል ጎሳ የተበላው ወጣት ሀኪም ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ከታሰረ በሁዋላ በእስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ ድብደባ ደርሶበት መሞቱን የፖሊስ ምንጮች ገልጸዋል።
ፖሊስ በበኩሉ ወጣቱ በራሱ ቲሸርት ታንቆ መሞቱን የገለጸ ሲሆን፣ የእስር ቤት ምንጮች እንዳሉት ግን ወጣቱ ከፍተኛ ደብደባ ደርሶበት ሊሞት ተቃርቦ እንደነበር፣ ፖሊስ እጁ እንደሌለበት ለማስመሰል ቲሸርቱን አውልቆ በወጣቱ አንገት ላይ በማሰር እራሱን እንደሰቀለ አድርጎ ለቤተሰቡ ሪፖርት አድርጓል።
ወጣቱ መጋቢት 25 ቀን 2006 ዓም መቀበሩን ለማወቅ ተችሎአል። ኢሳት በእስር ቤት ውስጥ የሚፈጸሙ አሰቃቂ ድብደባዎችን በተመለከተ መዘገቡ ይታወሳል። ሶስት ነጋዴዎችም እንዲሁ ፖሊስ ጋራጅ በተባለው እስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ ደብደባ ደርሶባቸው ራሳቸውን ስተው ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ ጋዜጠኛ ጀማል ዳውድ ከቀናት እስር በሁዋላ ተፈቷል። የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እስካሁን ድረስ ወደ ስፍራው በመሄድ እስር ቤቶችን አለመጎብኘታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።