ሰኔ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ሸብርና ወንጀልን ለመከላከል ይረዳል የተባለ በአገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ የመታወቂያ ካርድ ለመስጠት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ትናንት ለፓርላማ ቀረበ፡፡
በፍትህ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ም/ቤት ጸድቆ ለፓርላማ የቀረበው ረቂቅ ሕግ በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ ወጥ የሆነ፣የራሱ ሚሲጢራዊ ኮድ ያለው መታወቂያ በብሔራዊ ደረጃ ማዘጋጀት ያስፈለገው ሸብርና ወንጀልን ለመከላከልና ለምርመራ ተግባራት፣ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለግብር አከፋፈል፣ለፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት ጥቅም እንዲሰጡ ታስቦ ነው ይላል፡፡
አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ እነዚህ ተቋማት የዜጎችን መረጃዎች ማንንም ፈቃድ መጠየቅ ሳያስፈልጋቸው አሳልፈው የሚሰጡበትን አሰራር የተፈቀደ መሆኑን በረቂቅ አዋጁ ተደንግጓል፡፡
የብሔራዊ መታወቂያው የአገልግሎት ዘመን 10 ዓመታት መሆኑን የደነገገው ይኽው ረቂቅ አዋጅ ለብሔራዊ መታወቂያ ተሰብስበው በማዕከል የተደራጁትን ዝርዝር መረጃዎች መስረቅ፣ማበላሸት፣አሳልፎ መስጠት፣አላግባብ መጠቀም፣ከብሔራዊ ደህንነት አንጻር የሚያስከትለው አደጋ ከፍተኛ በመሆኑ ጥፋተኛው ከአስር እስከ ሃያ አምስት ዓመታት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡በተጨማሪም በምዝገባ ወቅት ሐሰተኛ መረጃ የሚሰጡ ሰዎች ከአንድ እስከ አምስት ዓመታት እስራትን ይከናነባሉ።
የብሔራዊ መታወቂያ አሰጣጥ ሥርዓት ለሃገሪቱ አዲስ ሥርዓት በመሆኑ የሕግ ማዕቀፉን ከማዘጋጀት ጎንለጎን ግብዓቶችን የሟሟላት ተግባር እየተከናወነ በመሆኑ በተመሳሳይ የሁለት ዓመት የመሸጋገሪያ ጊዜ ተቀምጦለታል፡፡
ይህ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማው ከመቅረቡ አስቀድሞ ባለፈው ሳምንት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሶፊያን አህመድ ለፓርላማው ባቀረቡት የ2005 ረቂቅ በጀት ሰነድ ላይ ለብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮጀክት 3 ሚሊየን 773 ሺ271 ብር በጀት አስይዘውለታል።
አዲሱ የመታወቂያ ወረቀት እደላ በቅርቡ እንደተረቀቀው የቴሌ ህግ ሁሉ የዜጎችን ማንነት ለመቆጣጠር ተብሎ የተዘጋጀ ነው የሚሉ አስተያየቶች ቀርበዋል። ገዢው ፓርቲ ዜጎችን ለማፈንና ለመቆጣጠር የ5 ለ1 አደረጃጀት፣ የጸረ ሽብር ህግ፣ የሚዲያ ህግ፣ የኤንጂኦ ህግ፣ የቴሌኮሚኒኬሽን አዋጅ፣ አሁን ደግሞ ብሄራዊ መታወቂያ ካርድ አሰራርን ተግባራዊ አድርጓል። ይህም ሆኖ ግን ህዝቡን ለመቆጣጠር እየተሳነው መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰኔ 30 ቀን 2004 ዓ.ም በይፋ የዚህን ዓመት ሥራውን የሚያጠናቅቀው የኢትዮጽያ ፓርላማ ባልተለመደ መልኩ ትናንት 12 ያህል አዋጆችን ተመልክቷል፡፡ለወትሮው በአንድ ቀን የፓርላማ ውሎ የሚታዩ አዋጆች ቢበዛ ቁጥራቸው ከሁለት አይበልጥም ነበር፡፡ፓርላማው የአንድ ፓርቲ የበላይነት የሰፈነበት ቢሆንም አዋጆችን በሰከነ መንፈስ እንኳን ማየት አለመቻሉ በዜጎች ሕይወት ጭምር መቀለድ ነው የሚል ትችትን አስከትሏል፡፡
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide