በሲዳማ ዞን እየተነሳ ባለው ተቃውሞ የመንግስት እጅ አለበት ተባለ

ሰኔ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአዋሳ ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጡት ለዘመናት ተቻችለው የኖሩ ህዝቦች እንዲጋጩ ለማድረግ የመንግስት ባለስልጣናት ሆን ብለው እየሰሩ ነው። ህዝቡ በኑሮ ውድነቱ፣ በመብት አፈናው እና በተለያዩ አስተዳደራዊ ችግሮች እየተማረረ፣ ከዛሬ ነገ ለውጥ ይመጣል እያለ በሚናፍቅበት በዚህ አስቸጋሪና አስፈሪ ወቅት፣ መንግስት የዋሳ ከተማን አስተዳደር እንደገና የህዝብ አጀንዳ አድርጎ በማቅረብ ግጭት እንዲነሳ መጣሩ ነዋሪዎችን አስቆጥቷል።

የዞኑ ባለስልጣናት የሚያስወሩት ዘርን ከዘር የሚያጋጭ ወሬ የከተማው ህዝብ የፍርሀትን ካባ እንዲደርብ እንዳደረገው ነዋሪዎች ይገልጣሉ። በዛሬው እለት ዳቶና  መምቦ በተባሉ አካባቢዎች ተማሪዎች ያሰሙትን ተቃውሞ ተከትሎ ዘርፊያ መካሂዱን፣ መኪኖች ታግተው መዋላቸውን ዘጋቢዎቻችን ገልጠዋል። በከተማዋ አሉ ሱቆች ዝርፊያ በመፍራት ተዘግተው መዋላቸውን ለማወቅ ተችሎአል። በዳቶና መምቦ አካባቢዎች የፌደራል ልዩ አድማ በታኝ ፖሊሶች በአስለቃሽ ጭስ ተቃውሞውን ለመቆጣጠር መቻላቸውን ውጥረቱ ግን አሁንም መኖሩን ዘጋቢዎች ገልጠዋል።

ግጭቱ  ከአዋሳ ከተማ እጣ ፋንታ አልፎ የዘር ጉዳይ እየሆነ መምጣቱ፣ የከተማውን ህዝብ ለሁለት መክፈሉም እየተነገረ ነው። የሲዳማ አገር ሽማግሌዎች ለዘመናት ተፈቃቅሮ የኖረውን ህዝብ የሚያበጣብጠው መንግስት በመሆኑ ተቃውሞው ሁሉ መንግስት ላይ እንዲሆን ወጣቶችን የማሳመን ስራ እየሰሩ ነው። የሲዳማ ተወላጅ ያለሆኑ የአዋሳ ነዋሪዎች ጥያቄው ከዘር አልፎ አገርአቀፍ አጀንዳ ይዞ ከመጣ ሊቀላቀሉዋቸው ዝግጁ መሆናቸውን እየገለጡ ነው።

አንድ ስሙን መግለጥ ያልፈለገ ወጣት ችግሩ እንዲህ በቀላሉ ይፈታል ብሎ እንደማያምን ገልጦ ፣ ተቃውሞውን ወደ ችግር ፈጣሪው መንግስት ማዞር ብቸኛ መፍትሄ ነው ብሎአል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide