<<ዝም ብላችሁ ጥሩ ነገር ብቻ ብትናገሩ አንሰማችሁም፤ እንደውም አጭበርባሪ ነው የምንላችሁ>> ሲሉ  ዶክተር ደብረጽዮን  ገብረሚካኤል -አርቲስቶችን ተናገሩ።

ጥር ፲፪(አስራ ሁለት ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ደብረጽዮን- ከአርቲስቶች ጋር  ባደረጉት ዝግ ስበሰባ የተናገሩት ነገር ተቀርጾ  በይፋ  በማህበራዊ  ሚዲያዎች የተለቀቀ ሲሆን፤ በንግግራቸው አርቲስቶችን ሲመክሩና፣ ሲያባብሉ እና  ሲገስጹ ተሰምተዋል።

<<በፌስ ቡክ የሚነገረንን ነገር እንሰማለን፤አርቲስቶች ሆዳሞች እንደምትባሉ እናውቃለን!>> ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፤ <<መለስን ሳይቀር የሚሳደቡ አሉ፤ መለስን ብቻ ሳይሆን ሁላችንንም ሲሰድቡን አይተናል>> ብለዋል።

<<እናንተም  የፈለጋችሁትን ነገር ንገሩን፤ ስድብም ከፈለጋችሁ ህሊናችሁ ከፈቀደ ስደቡን>> በማለት ለአርቲስቶቹ የተናገሩት ዶክተር ደብረጽዮን፤ <<ዝም ብላችሁ ጥሩ ጥሩ ነገር ብቻ ብትናገሩን አንሰማችሁም፤እንደውም  አጭበርባሪ ነው የምንላችሁ>>ብለዋቸዋል።

አክለውም፦<< እናንተ ባትነግሩንም ችግር እንዳለብን እኛ እናውቃለን፤ዝም ብሎ የሚቆልለንን ፊት ለፊቱ ባንናገረውም፤ ዞር ስንል ግን አጭበርባሪ ነው ማለታችን አይቀርም>>  ሲሉ ገስጸዋቸዋል።

ህወሀት የተመሰረተበትን 40ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ወደ ደደቢት አቅንተው የነበሩ አርቲስቶች በሙሉ ህወሀትን ሲያወድሱና ሲያሞካሹ፤ አርቲስት አስቴር በዳኔ ብቻ ጠንካራና ሞጋች ጥያቄ ማንሳቷ ይታወቃል።

አርቲስቷ ከ ኢሳት ጋር ባደረገችው ቃለ-ምልልስ ፦ያን ጥያቄ ካነሳች በሁዋላ ባለስልጣናቱ ሲያበረታቱዋት፤ ሌሎቹ የሙያ አጋሮቿ ግን እርሷ ጋር ላለመታየት እንደሸሿት ገልጻለች።

በአርቲስቶች በደረሰባት መገለል የተከፋችው አስቴር በዳኔ፤ የሙያ ጓደኞቿ  ያልሆኑን ከመሆን የአስመሳይነት ህይወት እንዲወጡ መክራለች።