ነሃሴ ፴(ሠላሳ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የፓርቲው የህግ ክፍልና የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ይድነቃቸው ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የመስተዳድሩ ባለስልጣናት ቀኑ የበአል ዋዜማ በመሆኑ እና የንግድ ድርጅቶችም እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት በመሆኑ ሰልፉን ለማስተናገድ እንደማይችሉ በመግለጻቸው ለማራዘም እንደወሰኑ ገልጸዋል።
አንድነት ፓርቲ መስከረም 5፣ 2006 ዓ/ም የጠራው የተቃውሞ ሰልፍ በመኖሩ በሳምንቱ ሰልፉን ለማካሄድ መወሰናቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ መስከረም 5 የጠራውን ሰልፍ 33ቱ ፓርቲዎች ድጋፋቸውን በመስጠት በጋራ ለመቀላቀል መወሰናቸውን ፓርቲውና 33ቱ ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ፓርቲዎቹ እንዳሉት ባለፉት 3 ወራት አንድነት ፓርቲ ያወጣው ህዝባዊ ንቅናቄ የመጀመሪያው ዙር መርሃ ግብር በአዲስ አበባ መስከረም 5ቀን 2006 በሚደረገው ታላቅ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ይጠናቀቃል ፡፡
ፓርቲው እንደሚለው የመስከረም 5ቱ ሰላማዊ ሰልፍ የ33ቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ይሁንታ ያገኘና ሰላማዊ ሰልፉን በባለድርሻነት የተሳተፉበት በመሆኑ ልዩ ነው።
ፓርቲው ባለፉት 3 ወራት የተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች ከፍተኛ መስዋትነት የጠየቁ ቢሆንም የተሳኩ ነበሩ ብሎአል። ፓርቲው በተንቀሳቀሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ ገዢው ፓርቲ ከህዝብ የተነጠለ መሆኑንና ህዝቡን እየመራሁ ነው የሚለው ህዝብን በማሸማቀቅ እንደሆነ መገንዘብ መቻሉንም ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።
በሌላ በኩል ደግሞ ፓርቲው በአዳማ/ናዝሬት በመጪው እሁድ ለሚያካሂደው ተቃውሞ የቅስቀሳ ወረቀቶችን ለመበትን የሚስለውን ፈቃድ ከወረዳ ባላስልጣናት ለማግኘት ዛሬ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። መንግስት በድብቅ ለሁሉም ወረዳዎች ባወረደው መመሪያ የፖለቲካ ድርጅቶች የተቃውሞ ሰልፍ ፈቃድ ቢያገኙ እንኳ፣ ከወረዳዎች የቅስቀሳ ወረቀቶችን ለመበትን ግድ ፈቃድ ማግኘት አለባቸው።
በትናንትናው እለት በቅስቀሳ ስራ ላይ የነበሩ የአንድነት አባላት ተይዘው ለአጭር ሰአታት ታስረው ተለቀዋል።
በሰማያዊ እና በአንድነት ፓርቲዎች ላይ እየደረሰ ያለው እስርና እንግልት በቀጠለበት ሰአት አለማቀፉ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል መንግስት በህገመንግስቱ የሰፈሩ የዜጎችን መብት እንዲያከብር ጠይቋል።