ሰማያዊ ፓርቲ፤ ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት የሚያስችለውን ጠቅላላ ጉባኤ የሚያካሂድበትን አዳራሽ በማጣቱ በጽ/ቤቱ ለማድረግ መገደዱን አስታወቀ

20 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-ከስድስት ወራት በፊት የአንድ ሺህ አምስት መቶ መስራች አባላትን የድጋፍ ፊርማ በማሰባሰብ የተቋቋመው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት የሚያስችለውን ጠቅላላ ጉባኤ የሚያካሂድበትን አዳራሽ  በማጣቱ  ጠቅላላ ጉባኤውን  በጽ/ቤቱ ለማድረግ መገደዱን አስታወቀ።

 ኢሳት ዜና:-ሰማያዊ ፓርቲ፤ ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት የሚያስችለውን ጠቅላላ ጉባኤ የሚያካሂድበትን አዳራሽ  በማጣቱ  በጽ/ቤቱ ለማድረግ መገደዱን አስታወቀ

ከፓርቲው አደራጆች አንዱ የሆኑት  የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት አባል አቶ አርአያ ጌታቸው ፤ ፓርቲው የመመስረቻ ጉባኤውን ለማካሄድ አቅዶ የነበረው ባለፈው እሁድ ታህሳስ 15 ቀን 2002 እንደነበር በማውሳት፤ “ሆኖም ህጋዊ አካል መሆናችሁን ከኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ አምጡ” በመባሉ፤ ጉባኤው ሳይካሄድ መቅረቱን ተናግረዋል።

በጥያቄው መሠረት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ የሕጋዊነት ደብዳቤ በማፃፍና የአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ፈቃድ ቢሮን ፈቃድ በመጠየቅ  ጉባኤውን በየካቲት 12 ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ  ለማካሄድ የትምህርት ቤቱን አስተዳደር ሲጠይቁ፦ ‘‘አዳራሹ ተከራይቷል’’ የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው  አቶ አርአያ ገልፀዋል።

 “ቀደም ሲል ትምህርት ቤቱ በታህሳስ ወር ሙሉ በሙሉ አዳራሹ አለመከራየቱን ገልፆልን ነበር” ያሉት አቶ አርአያ፤ ‘‘ ምርጫ ቦርድ በህገ-መንግስቱ መሠረት እየተንቀሳቀስን መሆኑን ገልፆ  ትብብር እንዲደረግልን ደብዳቤ ከፃፈልን በኋላ የስብሰባ አዳራሹን ለማሳወቅ ማዘጋጃ ቤት ደርሰን ስንመለስ፤ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር አዳራሹ መከራየቱን ገለፀልን’’ ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላ አማራጭ  መሰብሰቢያ  አዳራሽ መፈለግ  ከፓርቲው አቅም በላይ መሆኑን  የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው አቶ አርአያ  አስረድትዋል።

በዚህም ሳቢያ በተለይ ከክፍለ-ሀገር የመጡ የጉባኤው ተሳታፊዎች በመጉላላት ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ አርአያ፤በመሆኑም በመጪው እሁድ ታህሳስ 23 ቀን 2004 ግንፍሌ አካባቢ በሚገኘው ጽ/ቤታቸው ውስጥ በተጣበበ ሁኔታ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ መገደዳቸውን አስታውቀዋል።
ሰማያዊ ፓርቲ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ሲሆን፤ በዋናነት ለወጣቶችና ለሴቶች ቅድሚያ በመስጠት በምስረታ ላይ የሚገኝ ፓርቲ እንደሆነ ከሰንደቅ ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።

“አንድ የኢህአዴግ ሹመኛ   በመጽሀፍ መልክ ያሳተመውን  የውሸት ጥራዝ ሲያስመርቅ ፤በአገር ሀብት ላይ እየተፈፀመ ባለ የእከክልኝ – ልከክልህ ሙስናዊ ግንኙነት መነሻነት  ከወጣው ከፍ ያለ ገንዘብ በተጨማሪ- ሰፊው የሸራተን ላሊበላ አዳራሽ እስኪጠብብ ድረስ የኢህአዴግ  ሰዎች  በውስኪ  እየተራጩ በሚሰበሰቡባት አገር፤ በህግ የተመዘገበ አንድ የብዙሀን ፓርቲ- የመለስተኛ ትምህርት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ማጣቱ፤ በእርግጥም ፦’ይህ አገር የማን ነው?’የሚለውን ጥያቄ በተደጋጋሚ እንድናነሳ የሚያስገድደን ነው” ሲሉ አንድ የሰማያዊ ፓርቲ ጉባኤ ተሳታፊ ቅሬታቸውን ለኢሳት ገልፀዋል።