(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 8/2010)በመስቀል አደባባይ ሰኔ 16 በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ የአሰራር ክፍተት አሳይተዋል ተብለው ታስረው የነበሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ ጨምሮ 11 የፖሊስ አመራሮችም ዋስትና ተፈቀደላቸው።
አቃቤ ህግ የፖሊስ አመራሮቹ በዋስ ቢለቀቁ እንደማይቃወም ለፍርድቤቱ ገልጾ ነበር።
የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ በ15 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፈቅዷል።
ኮማንደር ገብረኪዳን አስገዶም፣ ኮማንደር ገብረስላሴ ታፈረ፣ ኮማንደር ግርማይ በርሄና ኮማንደር አንተነህ ዘላለምን ጨምሮ ሌሎች የአሰራር ክፍተት አሳይተዋል ተብለው የነበሩ ግለሰቦች ደግሞ ከ6 ሺህ ብር እስከ 9 ሺህ ብር በሚደርስ ዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ ውስኗል።
በዚህም የዋስትና ጉዳይን የሚመለከተው መዝገብ መዘጋቱን ነው ፍርድ ቤቱ ያስታወቀው።
የፖሊስ አመራሮቹ በሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት ኃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ሲካሄድባቸው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በተገኙበት መስቀል አደባባይ ሰኔ 16 በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ በርካታ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ይታወሳል።በዚሁ የሰኔ 16ቱ ቦንብ ፍንዳታ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው ጥላሁን ጌታቸው ግን ክስ ይመሰረትበታል ተብሏል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቦንቡን በማፈንዳት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በተሽከርካሪ ጭኖ ወስዷል ፣ እንዲሁም ቦንቡን ላፈነዳው ሰው የማቀበል ድርጊት ፈፅሟል በሚል የተጠረጠረው ብርሃኑ ጃፋርም ክስ ሊመሰረትበት መሆኑ ተገልጿል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን በተጠርጣሪዎች ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ አጠናቆ ለአቃቢ ህግ አስርክቧል።
አቃቢ ህግም ክስ ለመመስረት የ7 ቀን ክስ የመመስረቻ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ ተፈቅዶለታል።
ጥቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ ቦንቡን የወረወሩ ብቻ ሳይሆን ከጥቃቱ በስተጀርባ ድርጊቱን ያቀዱና ፋይናንስ ያደረጉም መጠየቃቸው አይቀርም ብለው ነበር። ከዚሁ ጥቃት ጋር በተያየዘ የድህንነት መምሪያ ሀላፊው አቶ ተስፋየ ኡርጌና ሌሎች ሁለት ባለደረቦቻቸው ታስረው ምረምራ እየተጣራባቸው ይገኛል።