አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ወደ ሃገሩ እንዲመለስ ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 8/2010)የመብት ተሟጋቹ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ወደ ሃገሩ እንዲመለስ ጥሪ ቀረበ ።

ለዚህ ታዋቂ አትሌት የጀግና አቀባበል ለማድረግ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዝግጅት ማድረጋቸውን ባወጡት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል።

በነሃሴ 2008 ዓም በብራዚል ሪዮ ዲጄነሮ በተካሄደው ኦሎምፒክ በማራቶን ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ያስገኘው  አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ  ውድድሩን ማሸነፉ ይታወሳል።

በዚሁ ወቅትም ሩጫውን ሲያጠናቅቅ በኢትዮጲያ የሚካሄዱ ግድያዎችን በአጠቃላይ የመብት ጥሰቶችን በመቃወም እጁን በማነባበር በዓለም ሕዝብ ፊት ባሳየው ተቃውሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታን ማግኘቱ ይታወሳል።

በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሱ ግፍ እና በደሎችን በአጠቃላይ የመብት አፈና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ ስም እና ዝናውን ያተረፈው ጀግናው አትሌት ፈይሳ ላለፉት 2 ዓመታት በአሜሪካ በሰደት ላይ ቆይቷል።

አትሌቱ ወደ ሃገሩ እንዲመለስ ዛሬ ጥሪ ያቀረቡት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሪሽን እና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ  ኮሚቴ ናቸው።

በአሜሪካ አሪዞና ግዛት ከባለቤቱ እና ከልጆቹ ጋር የሚኖረውን ጀግናው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ርሱም ወደ ሃገሩ የመመለስ ፍላጎት እንዳለው ለቢቢሲ ገልጿል።