ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች በሚል ወጪ ካደረገው 10 ሚሊዮን ብር መካከል 9 ሚሊዮን 989 ሺህውን ኢህአዴግ ወሰደው

የካቲት 14 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ምርጫ ቦርድ ለአስር ፓርቲዎች ለማከፋፈል በሚል  ከመንግስት ካዝና ወጪ ካደረገው 10 ሚሊዮን ብር መካከል 9 ሚሊዮን 989 ሺህውን ኢህአዴግ ወሰደው።

የተለመደ ህጋዊ ዘረፋ ወይም  የእንቁልልጭ ጨዋታ ነው ይሉታል-አንድ  የመድረክ ከፍተኛ አመራር ሰሞኑን ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ የፈፀሙትን ተግባር።

በቅድሚያ ምርጫ ቦርድ  10 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመደጎም 10 ሚሊዮን ብር ከመንግስት ካዝና ወጪ ማድረጉን አስታወቀ።

ይህ ሢሰማ፤አብዛኛው ገንዘብ የመንቀሳቀሻ አቅም ለሌላቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊውል ይችላል የሚል ጥርጣሬ የተሞላበት ግምት ማጫሩ አልቀረም።

ይሁንና  ብዙም ሳይቆይ ቦርዱ ገንዘቡን የማከፋፍለው የ 2002ቱን ምርጫ ውጤት ተከትሎ ፓርቲዎች በክልልና በተወካዮች ምክር ቤቶች ባገኙት መቀመጫ ልክ እያሰላሁ ነው አለ።

በ 2002ቱ ምርጫ ኢህአዴግ  በአገር አቀፍ ደረጃ ‘99 ነጥብ 6 በመቶ አሸንፌያለሁ’ ማለቱን ያፀደቀው፤ ይኸው ምርጫ ቦርድ መሆኑ ይታወቃል።

ቦርዱ ወጪ ያደረገውን 10 ሚሊዮን ብር በምክር ቤቶች ወንበር ልክ እያሰላ የሚያከፋፍል ከሆነ፤ከ ኢህአዴግ ውጪ በምክር ቤት ውስጥ ወንበር ያለው ፓርቲ እንደሌለ እየታወቀ ገንዘቡ ለ 10 ፓርቲዎች ይከፋፈላል መባሉ ግልጽ ሳይሆን ቆዬ።

ይሁንና የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ወይዘሮ የሺ ፈቃደ ትናንት ይፋ እንዳደረጉት ከ 10 ፓርቲዎች ውስጥ የተለያዩ ሰባት ፓርቲዎች ተደርገው በቦርዱ  የተቆጠሩት ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ ናቸው-የአርጎባ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት፣የሐረሪ  ብሔራዊ ሊግ፣የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፣የአፋር ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ፣የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲና የሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ።

እንደ ወይዘሮ የሺ ገለፃ፤ የአንድ የምክር ቤት ወንበር ዋጋ ፦3ሺህ 598 ብር ነው።

በዚህም መሰረት ከ 10 ሚሊዮኑ ውስጥ ኢህአዴግ ከ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ፤ አጋር ድርጅቶቹ ደግሞ ከ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ወስደዋል።

ከኢህአዴግና አጋሮቹ የተረፈችው 10ሺህ 794 ብር ወይም 0 ነጥብ 001 ፐርሰንቷ ነች ለሶስት የተቃዋሚ ፓርቲዎች የተከፋፈለችው -ለመድረክ፣ ለመ ኢአድና በአቶ አየለ ጫሚሶ ለሚመራው ቅንጅት።

በመሆኑም፤መድረክ አቶ ግርማ ሰይፉ በፓርላማ ባላቸው ወንበር፣መኢአድ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ባለው አንድ መቀመጫ እና በአቶ አየለ ጫሚሶ የሚመራው  ቅንጅት በአዲስ አበባ ምክር ቤት ባለው አንድ ቦታ፤ እያንዳንዳቸው የአንድ ወንበር ዋጋ 3 ሺህ 598 ብር ወይም በወቅቱ ምንዛሬ መሰረት 156 ዩሮ ደርሷቸዋል።

የመድረኩ አመራር እንደሚሉት፤ ይህ ገንዘብ ለፓርቲዎቹ ጽህፈት ቤቶች የአንድ ወር ኪራይ እንኳ አይሸፍንም።

ገንዘቡን ፓርቲዎቹ ለጽህፈት ቤት ሥራ ሊያውሉት ቢፈልጉ፤ አሁን ባለው የገበያ ዋጋ  20 እሽግ የደስታ ወረቀት ሊገዙበት ይችላሉ። መድረክ የደረሰውን ገንዘብ ይቀበል፤አይቀበል እስካሁን ማረጋገጥ አልተቻለም። ገንዘቡን መቀበሉን የገለፀው መኢአድም፤ ለመመለስ መወሰኑን አስታውቋል።

የድርጅቱ ዋና ፀሀፊ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ እንዳሉት፤መኢአድ ገንዘቡን የሚመልሰው ክፍፍሉ ኢ-ፍትሀዊ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፤ ምርጫ ቦርድ አነስተኛ መጠን ላለው ገንዘብ በውጪ ኦዲተር የተሰራ ሪፖርት እንዲቀርብለት ስለጠየቀም ጭምር ነው።

 የ3ሺህ 598 ብር ወጪን ኦዲት ለማስደረግ 15 ሺህ እና 20 ሺህ ብር ወጪ አድርገን ኦዲተር የምንቀጥርበት ምክንያት የለም የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ በዚህም ምክንያት ገንዘቡን እንዳለ ለመመለስ መወሰናቸውን ተናግረዋል።

“ይህ ክፍፍል ፍትሀዊ ነወይ?” ተብለው የተጠየቁት የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ፦” የተሰላው ፓርቲዎች በምክር ቤቶች ባላቸው ወንበሮች ስለሆነ፤ ምንም ማድረግ አይቻልም”ብለዋል።

በቅርቡ አቶ መለስ ዜናዊ በፓርላ ሪፖርት ሲያቀርቡ፤ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ መንግስት ድርጅታቸውን አስመልክቶ ትርጉሙ ግልጽ ያልሆነ የማንበርከክ ስትራቴጂ እየተከተለ እንደሚገኝ  መግለፃቸው ይታወሳል።

በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ አስተያየት የጠየቅናቸው የመድረክ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ሞጋ ፍሪሳ ለ6 ፓርቲዎች 3 ሺ 542 ብር ተሰጠ ተብሎ በመገናኛ ብዙሀን መናፈሱ ቀልድ ነው ብለውታል

ገንዘቡን በባንክ ቢያስገቡትም አንፈልግም ብለው መመለሳቸውን ዶ/ር ሞጋ ፍሪሳ ገልጠዋል ።

በፓርቲዎች መቀመጫ ቢሆን ኖሮ ቀድሞ በአቶ ልደቱ አያሌው አሁን በአቶ ሙሼ  ሰሙ የሚመራው ኢዴፓ ምንም የፓርላማ መቀመጫ ሳይኖረው 300 ሺ ብር መሰጠቱትን አሰራሩ ትክክል አለመሆኑን ያሳያል ብለዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide