መጋቢት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ላለፉት 13 ወራት ዘወትር አርብ ተቃውአቸውን ያለመሰልቸት በጽናት እያሰሙ ያሉት ሙስሊም ኢትዮጵያውያን፣ ዛሬም ተመሳሳይ ተቃውሞ ሲያሰሙ አርፍደዋል።
በሻሸመኔ፣ አርሲ፣ ደሴ ፣ ስልጤ እና ሌሎችን ከተሞች በድምጽ ተቃውሞዎች ሲካሄዱ፣ በአዲስ አበባ ደግሞ ወትሮ ተቃውሞ የሚደረግበት ታላቁ አንዋር መስኪድ ጭር ብሎ ፒያሳ የሚገኘው ኑር መስጊድ በሰዎች ተጨናንቆ አርፍዷል።
ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ የሚገኙት የድምጻችን ይሰማ አመራሮች እንዲፈቱ፣ መንግስት ለጥያቄያቸው መልስ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በአገር ቤት የሚደረገውን ተቃውሞ በመደገፍ በስዊድን የሚገኙ ሙስሊም እና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን በጋራ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል።
ዛሬ በስቶክሆልም በኢትዮጵያ ቆንስላ ፊት ለፊት በተካሄደው ተቃውሞ ፣ መንግስት ለዘመናት ተከባብሮ የኖረውን ሙስሊም እና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያንን በማጋጨት አገሪቱን ለማጥፋት የሚያደርገውን ሩጫ በጽኑ አውግዘዋል።
“ሁላችንም አቡበክር ነን፣ ሁላችንም ያሲን ኑሩ ነን፣ ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ፣ በጅሀዳዊ ሀረካት ሙስሊም እና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ማጋጨት አይቻልም” የሚሉ መፈክሮች ቀርበዋል።