ኢህአዴግ ለ2002ቱ ምርጫ ከ56 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ማውጣቱን አንድ ሪፖርት አጋለጠ

መጋቢት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-ኢህአዴግ በዓለም የምርጫ ታሪክ እጅግ አስደናቂ በሆነ መልኩ 99 ነጥብ 6 በመቶ በማሸነፍ ወደ አውራ ፓርቲ ተሸጋግሬበታለሁ ባለው የ2002ቱ ምርጫ በድምሩ ከ56 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ከግንባሩ የተገኘ ሪፖርት አመለከተ፡፡

ይህ ገንዘብ የኢትዮጵያ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ለምርጫ ቦርድ በቀጣይ ወር ለሚያካሂደው የአካባቢና የአዲስአበባ ምርጫን ጨምሮ ለመደበኛ በጀት ከፈቀደለት 19 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ጋር ሲነጻጸር እጅግ የላቀ መሆኑን ምንጫችን ጠቅሶአል፡፡

ኢህአዴግ በ1997ቱ ምርጫ ክፉኛ ሽንፈት ከገጠመው በኋላ የተካሄደው የ2002ቱን ምርጫ በአሸናፊነት ለመውጣት ነዋሪዎችን አንድ ለአምስት በሚባለው አደረጃጀት ከማዋቀሩም ባሻገር ለሚካሄዱ ስብሰባዎች አበልን እና የትራንስፖርት በመክፈል ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ወጪ ማውጣቱን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡

በዚሁ መሰረት ግንባሩ በ2001 ዓ.ም 29 ሚሊየን 258 ሺ 585 ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በዚሁ ዓመት ከ2002ቱ ምርጫ ጋር ተያይዞ 23 ሚሊየን 802 ሺ 034 ሳንቲም ወጪ ማድረጉን ይገልጻል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በ2002 ዓ.ም ግንባሩ 53 ሚሊየን 224 ሺ  756 ብር ከ04 ሳንቲም ገቢ ያገኘ ሲሆን ለምርጫው ብቻ በዚሁ ዓመት  32 ሚሊየን 269 ሺ 759 ብር ከ13 ሳንቲም ወጪ አድርጌአለሁ ብሏል፡፡ ገንዘቡ ለአራቱ አባል ድርጅቶች ለዚሁ የምርጫ ስራ እንዲያውሉት የተበተነ ነው፡፡

 

የግንባሩ የገንዘብ ምንጭ ተብሎ ከተቀመጠው ውስጥ የኢህአዴግ ደጋፊ ባለሃብቶች መዋጮ 54 በመቶ ድርሻ የያዘ ሲሆን 24 በመቶ ከአባል ድርጅቶች የተገኘ እና ቀሪው ከአዲስ ራዕይ መጽሔት ሸያጭ፣ከአሮጌ ንብረቶች ሸያጭ፣ከአባላት መዋጮ የተገኘ መሆኑን ጠቅሶአል፡፡

 

ምርጫ ቦርድ ዘንድሮ ለሚያካሂደው ምርጫ በጠቅላላው 19 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የተበጀተለት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለፍትሐዊ ምርጫ በሚል የተያዘው በጀት 13 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ብቻ ነው፡፡

 

በ2002ቱ ምርጫ ተቃዋሚዎች ከምርጫ ቦርድ የተቀበሉት ገንዘብ ከ 3ሺ ብር አይበልጥም ነበር።

ኢህአዴግ በአገሪቱ ቁጥር አንድ ነጋዴ ፓርቲ ቢሆንም፣ ለምርጫ ማስፈጸሚያ አብዛኛውን ወጪውን የሚሸፍነው ከነጋዴዎች በማስፈራራት በሚቀበለው ገንዘብ መሆኑን ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ። ለኢህአዴግ ገንዘብ ለማዋጣት ፈቃደኛ ያልሆኑ ነጋዴዎች፣ በተለያዩ አስተዳደራዊ ጫና ድርጅቶቻቸውን እየዘጉ ስደትን መምረጣቸው ይታወቃል።

 

በተመሳሳይ ዜና ደግሞ የኢህአዴግ መንግሥት ቀደም ሲል በ1997 ዓ.ም የምርጫ ወቅት የተቃዋሚ ፓርቲ የምርጫ ታዛቢ የነበሩና በአሁኑ ጊዜ አባላቱ እንዲሆኑ ያደረጋቸውን ግለሰቦች በመጪው ሚያዚያ ወር ላይ ለሚካሄደው የአዲስ አበባ እና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ላይ ነፃ ታዛቢ እንዲመስሉለት ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ከአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽቤት ያገኘነው መረጃ ይገልፃል፡፡

እነዚህ ግለሰቦች፣ በመንግስት ቤት፣ በመንግስት ሥራ፣ እና በመደራጀት እንቅስቃሴ ውስጥ የጥቅም ተጋሪዎች እንዲሆኑ የተደረጉ ናቸው ብለዋል፡፡

በየአካባቢው የሚታወቁ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ባለሃብቶች እና ካድሬ የሃይማኖት አባቶች የምርጫ ታዛቢነት ጥሪ በኢህአዴግና በምርጫ ቦርድ በኩል እየቀረበላቸው መሆኑንም ታውቋል፡ ፡

ቀበሌዎች  የሚተማመኑባቸውን ሰዎች ለምርጫ ታዛቢነት በመጠቆምና ጠርቶ በማነጋገር ሥራ ላይ መጠመዳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡