መድረክ የፖለቲካ ተጽእኖው በረታብኝ አለ

መጋቢት ፳፭ (ሃይ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ  ጎተራ አካባቢ በሚገኘው የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ አዳራሽ ቅዳሜ መጋቢት 22 ቀን 2004 ዓም ስብሰባ ቢጠራም፣ አዳራሹን ያከራየው ድርጅት በመጨረሻ አዳራሹን እንደማያከራይ በመግለጡ በኑሮ ውድነቱና በአዲሱ የሊዝ አዋጅ ዙሪያ ሊካሄድ የነበረውን ስብሰባ ለመሰረዝ ተገዷል። የመድረክ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ሞጋ ፍሪሳ መድረክ ስብሰባ ለማካሄድ ከመንግስት ፈቃድ ማግኘቱን እና አስፈላጊውን ክፍያ መፈጸሙን ተናግረው ፣  ከበላይ አካል በመጣ ትእዛዝ ስብሰባው እንዳይካሄድ መደረጉ እንዳሳዘናቸው ገልጠዋል።

የሰላማዊ ታጋዮች ሆናችሁ የስብሰባ አዳራሽ ካላገኛችሁ ትግላችሁን በምን መልኩ ነው ለመቀጠል ያሰባችሁት ተብለው ለተጠየቁት ዶ/ር ሞጋ ፍሪሳ የሚከተለውን መልሰዋል (2፡25-2፡56)”

መድረክ የምርጫ ስነምግባሩን ባለመፈረሙ በመንግስት እንደ ሽብረተኛ ድርጅት እንደሚታይ፣ ያም ሆኖ የምርጫ ስነምግባር ስምምነቱን የፈረሙትም ድርጅቶች ቢሆኑ ከስምምነቱ ምንም ጥቅም ያገኙ ባለመሆናቸው ስምምነቱን መፈረሙ ትርጉም የለውም ሲሉ ሊቀመንበሩ አክለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የኦፌዴን አመራር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ በቀረበባቸው የሽብርተኝነት ክስ ጥፋተኛ ተብለው እንዲከላከሉ ፍርድ ቤት ወስኖአል።

አቶ በቀለ ገርባ የታሰሩት የአረቡ አብዮት በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች መነሳቱን ተከትሎ፣ ተመሳሳይ አመጽ ሊያስነሱ ይችላል የሚል ስጋት አይሎ በነበረበት ወቅት ነው። አቶ በቀለ የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል።

_______________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide