የአፋር ህዝብ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ተፋጧል ነፍሰ ጡሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ታስረዋል

መጋቢት ፳፬ (ሃይ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የመለስ መንግስት በአፋር አካባ ቢ የጀመረው የስኳር ልማት ፕሮጀክት ከተወላጆች ከፍተኛ ተቃውሞ ስለገጠመው ልዩ ሀይሉን እና የመከላከያ ሰራዊት አባላቱን በአካባቢው አሰማርቶ ተወላጆችን በማሰር፣ በመድብደብና በማሰቃየት ላይ ነው።

የአካባቢው ተወላጆች ለኢሳት እንደገለጡት መንግስት በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ሳይፈቅዱ አካባቢውን ማረስ መጀመሩን የአካባቢው ሰዎች መቃወም በመጀመራቸው ሁለት ነፍሰ ጡሮችን ጨምሮ 8 ሴቶችና ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወንዶች ታስረው ተይዘዋል። ከታሰሩት መካከልም ከፍተኛ የሆነ ድብደባ የተፈጸመባቸው አሉ።

የአካባቢው ተወላጆች ዶዘሮች ቤታቸውን እንዳያፈርሱባቸው ለመከላከል መሞከራቸውን ተከትሎ መንግስት ልዩ ሀይሉን ማሰማራቱን፣ እያንዳንዱ ዶዘር ቢያንስ በሁለት ታጣቂ እየተጠበቀ መገኘቱንና የአካባቢው ሰው የዶዘሮችን እንቅስቃሴ ለማስቆም ቢሞክር ወታደሮቹ እርምጃ እንዲወስዱ መታዘዛቸውን ነዋሪዎች ገልጠዋል።

አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ነዋሪ እንዳሉት የመንግስትን እርምጃ በመቃወማቸው በጥይት ተመትተዋል።

ከሰባ ሺ በላይ የአፋር ህዝብ ይፈናቀላል ተብሎ እንደሚገመት ነዋሪዎች የገለጡ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ መንግስትና ህዝብ ተፋጥጠው እንደሚገኙ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ አንድ ሌላ ነዋሪ ገልጠዋል።

የአፋር የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ድርጅት ሀላፊ የሆኑት አቶ ገአስ አህመድ ኑር በበኩላቸው መንግስት በህዝቡ ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አውግዘዋል።

አቶ ገአስ እንዳሉት የአለማቀፉ ማህበረሰብ በአፋር ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ሊያስቆም ይገባዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው የህዝብ መፈናቀል በመላ አገሪቱ ቁጣን እየቀሰቀሰ ነው። በደቡብ ኦሞ ከ200 ሺ በላይ ህዝብ መፈናቀሉን ተከትሎ ከፍተኛ የጸጥታ መደፍረስ እየታየ ነው። በጋምቤላም እንዲሁ በክልሉ ለሚታየው ተደጋጋሚ የጸጥታ ችግር ዋናው መንስኤ የህዝብ መፈናቀል ነው።  በሰሜን ጎንደር በዋልድባ አካባቢ፣ በደቡብ ክልል በቤንቺ ማጂ ዞንም እንዲሁ በርካታ የአማራ ተወላጆች መፈናቃለቸው ይታወቃል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide