መንግስት የአወልያን ሰላማዊ ተቃውሞ ወደ ግጭት ለመለወጥ እየጣረ ነው ተባለ

የካቲት 22 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአወሊያ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና በትምህርት ቤቱ አስተዳደር መካከል ተከስቶ ወደ ብዙሀኑ ሙስሊም የተሸጋገረውና  ስምንት ሳምንታት  ያስቆጠረው ተቃውሞ  መፍትሔ ሳያገኝ፤ ይልቁንም ውሎ ሲያድር እየጋለና እየተጋጋመ መጥቶ እጅግ አሣሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ብዙሀኑ ሙስሊሞች ሳምንታት በዘለቀው ተቃውሟቸው   የሙስሊሙን ህብረተሰብ እንዲመሩ በነሱ ምርጫ ሳይሆን በመንግስት ውክልና የተቀመጡት የመጂሊስ አመራሮች እንዲነሱላቸው እንዲሁም፤  መንግስት ፦“አህባሽ” የተሰኘውንና ከውጪ የመጣ ነው ያሉትን የሀይማኖት አስተምህሮ ያለ እምነትና ፍላጎታቸው በ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ በሀይል ለመጫን የሚያደርገውን ሙከራ እንዲያቆም  ሲጠይቁ ቆይተዋል።

“መንግስት ለነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ  አልሰጠንም፤ ይልቁንም  “የህገ መንግስታዊ መብታችን ይከበርልን “ጥያቄያችንን  ወደ ሌላ ያልተፈለገ አቅጣጫ በመጠምዘዝ  ችግሩን የሚያባብስ አደገኛ መንገድ እየተከተለ ነው” ይላሉ- የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ወኪሎች።

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ሰሞኑን በደብረዘይት በተካሄደ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊዎች ስልጠና ላይ ተገኝተው ፦” በኢትዮጵያ፤ህጋዊውን መንግስት ገልብጦ የሸሪያ መንግስት ለማቋቋም ዕቅድ ነድፎ ከ 30 ዓመታት በላይ ሲንቀሳቀስ የነበረ አክራሪ ቡድን አለ፤ ይህ ቡድን በውጪ ሀይሎች የገንዘብ ድጋፍ  ፍላጎቱንና እምነቱን በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ በሀይል በመጫን፣መስጊዶችንና ቤተ-ክርስቲያኖችን በማቃጠል የራሱን መንግስት በሀይል ለመመስረት የተደራጀ ነበር”ብለዋል።

ከብዙሀኑ ሙስሊም ተወካዮቹ አንዱ  ግን፤ ይህ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ አባባል፦”ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ፤ይሏታል ጅግራ! እንዳይሆን ያሰጋኛል”በማለት ነው ለ ኢሳት የተናገሩት።

 መንግሰት ብዙሀኑ ሙስሊም የመብት ጥያቄዎችን ማንሳታቸውን ተከትሎ አንድ ጊዜ አሸባሪዎችን ይዣለሁ፤ ሌላ ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ ሀይማኖትን አስታክኮ ከሚሰማው ውዥንብር ራሳችሁን አግልሉ” እያለ ህዝቡን ሲያሸብር ከርሟል”ያሉት እኚሁ የብዙሀን ሙስሊም ወኪል፤ የዶክተር ሽፈራው ማሣሰቢያም የዚያው ቅጥያ ይመስለኛል”ብለዋል።

“ ጥያቄያችን፤ህገ-መንግስታዊ መብታችን ይከበር፤ ባልመረጥናቸው ሳይሆን በመረጥናቸው ሰዎች እንተዳደር፣ መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ ገብቶ ያልተቀበልነውን እምነት አይጫንብን የሚል ግልፅና ቀጥተኛ ነው።መንግስት ይህን ቀላል ጥያቄ መፍታት ተስኖት ነገሩን እያጓተተና እያጠላለፈ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሲመራው ማዬት እጅግ ያሳዝናል”ሲሉም አክለዋል።

በተለይ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ፦የራሱን ፍላጎት በነባሩ ሙስሊም ማህበረሰብ ላይ በሀይል ለመጫን የሚንቀሳቀስ አክራሪ ቡድን ተደርሶበታል ያሉትን ለማመን ያስቸግራል” ያሉት እኚሁ ተወካይ፤ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ብዙሀኑ ሙስሊም የማይቀበለውን “አህባሽ” የተባለ አስተምህሮ በሀይል ሊጭንብን እየተንቀሳቀሰ ያለው ራሱ መንግስት እንደሆነ ግልጽ ሆኗል ብለዋል።

አቶ መለስ ዜናዊም ከሁለት ዓመታት በፊት ሀይማኖታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው ከወጣቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነባሩን የኢትዮጵያ እስልምና በሀይል ለመቀየር የሚፈልጉ ቡድኖች  እርምጃ እንደሚወሰድባቸው መናገራቸውን   የብዙሀኑ ወኪል አስታውሰዋል።

በጣም አሳዛኙ ነገር፤ ዛሬ ከሁለት ዓመታት በሁዋላ የብዙሀኑን ሙስሊም እምነት በሀይል ለማስለወጥ እየተንቀሳቀሰ ያለው የብዙሀኑ ሙስሊም ጠበቃ ነኝ ሲል የነበረው የራሳቸው የአቶ መለስ መንግስት መሆኑ ነው ብለዋል -እኚሁ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የብዙሀኑ ወኪል።

 መንግስት  ሙስሊሞች ላነሱት ጥያቄ መልስ ባለመስጠቱም በየሳምንቱ ከ”ጁምአ” ጸሎት በሁዋላ የሚደረገው ተቃውሞ እያየለ መጥቶ ባለፈው ሳምንት አርብ ከ 120 ሺህ በላይ የሚሆኑ አማኞች ለ 7 ሰ ዓታት የቆየ ተቃውሞ ማሰማታቸው ይታወሳል።

ጥያቄያቸው ተገቢውን ምላሽ እስኪያገኝ ድረስም፤ ተቃውሟቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።ለወራት የዘለቀው ተቃውሞ በምን መልክ ይቋጭ ይሆን የሚለው ጉዳይ፤ የብዙዎች መነጋገሪያ መሆኑን ቀጥሏል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide