የአማራ ተወላጆች ከደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች ለቀው እየወጡ ነው

የካቲት 21 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአማራ ተወላጅ አርሶአደሮች ከደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች ለቀው እየወጡ ነው፣ በአርሶአደሮች ላይ ዘግናኝ ደርጊትም እየተፈጸመባቸው ነው

በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ለረጅም አመታት ይኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጆች ከክልሎች ነቅለው እንዲወጡ እየተገደዱ መሆኑንና በርካታ አርሶአደሮች ለዘመናት ያፈሩትን ሀብትና ጥሪት እየተነጠቁ ለስቃይ እየተደራጉ መሆኑን አንድ የመኢአድ የአመራር አካል ለኢሳት ተናግረዋል።

አቶ ያሬድ ግርማ ለኢሳት እንደገለጡት በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ የአማራ ተወላጆች ፣ ክልሎቹን በአስቸኳይ ለቀው ካልወጡ ሀብትና ንብረታቸውን ከመቀማታቸው በተጨማሪ ይደበደባሉ ይታሰራሉ።

በክልሎች የሚኖሩ አርሶአደሮች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለፌደራል መንግስት ባለስልጣናትና ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች አቤት ቢሉም የሚሰማቸው አላገኙም። ብዙዎቹም በአዲስ አበባና በክልሎች በችጋር እያለቁ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሪፖርተር በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን ጉራፋርዳ ወረዳ የሚኖሩ በርካታ የአማራ ክልል ተወላጆች ሕገወጥ ሰፋሪዎች ናችሁ በሚል እስከ የካቲት 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ የተላለፈላቸው መሆኑን ዘግቧል

በህጋዊ መንገድ ለአመታት የኖሩት አርሶአደሮች  ባልጠበቁትና ባላሰቡት ሁኔታ ሀብትና ንብረታቸውን ጥለው አካባቢውን እንዲለቁ ትዕዛዝ እንደተላለፈላቸው የማዘዣ ወረቁትን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

በርካታ የአማራ ክልል ተወላጆች በሕጋዊ መንገድ ለተረከቡት መሬት ግብር ሲከፍሉ መቆየታቸውን የሚያረጋግጥ የግብር ካርድ እንዲሁም የወረዳና የቀበሌ አመራሮች ‹‹መሬት ይሰጣቸው›› ብለው ትዕዛዝ ያስተላለፉበት ደብዳቤ በማስረጃነት ቢኖራቸውም፣ ህገወጥ ነዋሪ ናችሁ በሚል አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል።

የቤንች ማጂ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ዓለማየሁ አይበራ  ከአንድ ዓመት በፊት በደቡብ ክልል የሚኖሩ ሕገወጥ ሰፋሪዎችን በሚመለከት የአማራ ክልልና የደቡብ ክልል ኃላፊዎች ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ የአማራ ክልል የራሱን ዝግጅት በማድረግ ከ800 በላይ የሚሆኑ በደቡብ ክልል ይኖሩ የነበሩ ሰፋሪዎች ወደ ባህር ዳር እንዲመለሱ መደረጉን ገልጠዋል።

‹‹ከአማራ ክልል ወደ ደቡብ ክልል የሚደረግ ሰፈራ የለም፤ ወረዳዎች ላይ የምትፈርደው ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም፣ መመለስ ያለበት ሰው ካለ መመለስ አለበት፡፡ ይሄ የእኛም የክልሉም አቋም ነው፡፡ ነዋሪ ያልሆነን ሰው ሥርዓት በሌለው ሁኔታ ተቀብለን ልናሰፍር አንችልም፤›› በማለት ለጋዜጣው ተናግረዋል።

እንደጋዜጣው ዘገባ ጉራፋርዳ ወረዳ በሚገኙ 22 ቀበሌዎች ውስጥ ከአማራ ክልል መጥተው ለረጅም ዓመታት ኑሮአቸውን በዚያው የመሠረቱ ከ78 ሺሕ በላይ ዜጐች ይገኛሉ።

 ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር በተላለፈ ቀጥተኛ መመርያ ከ1999 ዓ.ም. በኋላ ከሰሜን አካባቢ የመጡ ሰፋሪዎች ወደመጡበት እንዲመለሱ መታዘዙንና  ውሳኔን ተከትሎ በአለንጋ ቀበሌ ማርያም ሰፈር በሚኖሩ ሰዎች ላይ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን የወረዳው የገጠር ልማት ምክትል ኃላፊ ማዘዛቸው ተዘግቧል፡፡  በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የዘር ፖለቲካ አስከፊ ደረጃ ላይ እየደረሰ መምጣቱን ብዙዎች ይስማማሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide