መንግስት አቶ መለስ ዜናዊ መታመማቸውን አመነ

ሐምሌ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የብሉምበርጉ ዊሊያም ዳቪድሰን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑትን አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝን ጠቅሶ እንደዘገበው አቶ መለስ የአፍሪካን ህብረት እና ሌሎች ስብሰባዎችን መሳተፍ ያልቻሉት በህመም ምክንያት ነው።

“ለህይወት በሚያሰጋ በሽታ አልታመሙም፣ እንደማንኛውም ሰው ህክምና ማግኘት አለባቸው፣ ህክምናቸውን ጨርሰውም በቅርቡ ወደ አገር ቤት ይመለሳሉ ” በማለት አቶ ሀይለማርያም ተናግረዋል።

ከሳምንት በፊት የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል ስለ አቶ መለስ መታመም ተጠይቀው፣  አቶ መለስ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ፣ የስራ መብዛት ከመገናኛ ብዙሀን እንዳራቃቸው እና ታመዋል በማለት የሚያስወራው ኢሳት መሆኑን ገልጠው ነበር።

አቶ መለስ በሳይንሱ ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት ላስመሰገቡ ኢትዮጵያውያን ሽልማት መስጠት ባለመቻላቸው እንዲሁም ፓርላማው ጊዜውን ጠብቆ ባለመዘጋቱ በአቶ መለስ ጤና ዙሪያ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ቆይቷል።

ጉዳዩን በቅርብ ሲከታተሉ የነበሩ የግንቦት7 ራዲዮ ጋዜጠኞች አቶ መለስ ቤልጂየም በሚገኘው ሴንት ሉክ ሆስፒታል ሲታከሙ መቆየታቸውን፣ ህመማቸው ከፍተኛ በመሆኑም በህይወት የሚቆዩበት ጊዜ እንደተነገራቸው ዘግበው ነበር።

አቶ መለስ በሊቀመንበርነት የሚመሩት ኔፓድ በአዲስ አበባ ስብሰባውን ሲያካሂድ አቶ መለስ አለመገኘታቸውን ተከትሎ  የሴነጋሉ መሪ የሖኑት ማኪ ሳል የአቶ መለስን መታመም ይፋ አድርገዋል።

እሁድ እለት በተከፈተው የአፍሪካ ህብረት ስበሰባ ላይ አቶ መለስ በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ሲጠበቅ እንዲሁም ምሽት ላይ የእራት ግብዣ እንደሚያደርጉ ሲነገር ሳይገኙ ቀርተዋል።

ዋሽንግተን ፖስትን የመሳሰሉ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙህን ዜናውን እየዘገቡ ባለበት ወቅት ፣ በቅርቡ የተመሰረተውና በዶ/ር ፍስሀ እሸቱ የሚመራው የኢትዮጵያ የሽግግር ካውንስል፣ ከኢህአዴግ የቅርብ ሰዎች ያገኘሁት መረጃ ነው በማለት አቶ መለስ ማረፋቸውን ገለጠ።

 

አንድ የግብጽ የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን አዲሱ የግብጽ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ሞርሲ አቶ መለስ በጀርመን ሀገር የተሳካ ቀዶ ጥገና ማድረጋቸውን በማስመልከት የመልካም ምኞት መልክት እንደሰደዱላቸው ዘግቧል።

በሌላ በኩል ደግሞ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ በሆነው አይጋ ፎረም ላይ የወጣ አቶ መለስን የሚዘክር የሚመስል አንድ ጽሁፍ አቶ መለስ አንድም አርፈዋል ሌላም ከእንግዲህ ወደ ስልጣን ተመልሰው ስራ መስራት በማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል የሚል ጥርጣሬ አሳድሯል።

አቶ መለስ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ እርሳቸውን ተክተው በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ ንግግር ለማድረግ የሚያግዳቸው ነገር አይኖርም ነበር የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ባለበት ወቅት፣ አቶ ሀይለማርያም ከአሁን ጀምሮ በአለማቀፍ መድረኮች ላይ ንግግር እንዳያደርጉ በህወሀት ፖሊት ቢሮ አባላት መታገዳቸውን የሚገልጥ መረጃ መሰራጨት ጀምሮ ነበር።

ከዚህ ቀደም ይደረግ እንደነበረው አቶ መለስ በፓርላማው መዝጊያ ወቅት ተገኝተው ስለ አገሪቱ በጀትና ሌሎች ከፓርላማ አባላት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ ይሰጡ ነበር። ዛሬ በተካሄደው የፓርላማ ስብሰባ አቶ መለስን በመተከታኢ ስለበጀቱ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ሶፍያን አህመድ ናቸው።

የአቶ መለስ ዜናዊ መታመም እውነት መሆኑን፣ መንግስት ለማመን ቢገደድም፣ የህመማቸው ደረጃ ምን ያክል እንደሆነ በውል የታወቀ ነገር የለም። ይሁን እንጅ ህመማቸው ጠንካራ ባይሆን ኖሮ በውጭ አገር እጅግ ውድና ዘመናዊ በሆነ ሆስፒታል ለአመታት አይታከሙም ነበር የሚሉ አስተያየቶች አሉ።

አቶ መለስን ህመም ተከትሎ በአማራ ክልል ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን ምንጮች ገልጠዋል። ሰሞኑን ከባህርዳር እስከ አዲስ አበባ ባለው መንገድ ተጓዦች በተደጋጋሚ ከመኪና እየተወረዱ ሲፈተሹና ሲጠየቁ ሰንብቷል።

የክልሉ የኢህአዴግ ባለስልጣናትም ሆኑ ደጋፊዎች በስራ ገበታቸው ላይ አዘውትረው እንደማይገኙና ከፍተኛ የሆነ ግራ መጋባት መፈጠሩን ምንጮቻችን ገልጠዋል።

የአቶ መለስ የጤንነት ሁኔታ አነጋጋሪ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ እርሳቸውም ማን ይተካቸዋል የሚለውም ሌላ መሰረታዊ ጥያቄ ያስነሳ ጉዳይ ሆኗል።

አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ አቶ መለስን ሊተኩ እንደማይችሉ ፍንጮች መታየት መጀመራቸውን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚዎች ወደ ህብረት እንዲመጡ አንዳንድ አለማቀፍ መንግስታት ጥረት መጀመራቸውን ነው ለኢሳት የደረሰው መረጃ የሚያመለክተው።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide