መንግስት በውጭ የሚኖረውን ዲያስፖራ ለመያዝ ይረዳኛል በሚል ከጀመራቸው የቤት ልማት ፕሮግራም ውስጥ 40 በ60 በሚባለው ፕሮግራም የሚገነቡ ቤቶች ከምርጫ 2007 በፊት ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ ሳይችል ቀረ፡፡

መጋቢት ፬(አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከሚቀጥለው ሳምንት ከመጋቢት 10 እስከ 13 ድረስ ባሉት ቀናት የአዲስአበባ አስተዳደር 20 በ80 ተብሎ

የሚታወቀውን የኮንዶሚኒየም 35 ሺ ቤቶች ዕጣ በማውጣት ለእድለኞች ለማስተላለፍ ያቀደ ሲሆን በዚህ የዕጣ አወጣጥ ፕሮግራም ላይ 40 በ 60 የሚባለውና አብዛኛው ዲያስፖራ ተመዝግቦበታል የተባለው ዕጣ እንደማይወጣ ታውቆአል፡፡

የአዲስአበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ሰሞኑን በተካሄደው የአስተዳደሩ ም/ቤት ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እንደጠቆሙት 1 ሺ 200 ያህል 40 በ 60 የተገነቡ ቤቶች ግንባታቸው ባለመጠናቀቁ በመጪው ሰኔ ወር ለማስተላለፍ ዕቅድ ተይዞአል፡፡

ለዚህ ለ40 በ 60ፕሮግራም  የተመዘገበው 164 ሺ 779 ሕዝብ ሲሆን ለአንድ መኝታ ቤት በየወሩ 1 ሺ 33 ብር፣

ለሁለት መኝታ ቤት በየወሩ 1 ሺ 575 ብር፣ ለሶስት መኝታ ቤት በየወሩ 2 ሺ 453 ብር እየቆጠበ ይገኛል፡፡ ይህ የቤት ልማት ፕሮግራም ከሌላው ለየት የሚያደርገው መንግስት ምንም ዓይነት ድጎማ የማያደርግበትና ዕድለኞች የቤቱን ሙሉ ወጪ ከፍለው እንዲወስዱ የታሰበ መሆኑ ነው፡፡

በዚሁ መሰረት 40 በመቶ ባለዕድለኛው ሲከፍል 60 በመቶውን ከባንክ በሚገኝ ብድር ባለቤት ለማድረግ ታስቦ የተጀመረ ቢሆንም፣ በኃላ ላይ የገንዘብ እጥረት በማጋጠሙ ምክንያት ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ መቶ በመቶ ቅድሚያ ለከፈለ ቅድሚያ ያገኛል የሚል በአንድ ወቅት መግለጫ መስጠታቸው ብዙዎችንተስፋ አስቆርጦአል፡፡

የአስተዳደሩ ምንጮች እንደሚናገሩት ይህም ሆኖ በርካታ ሰዎች መቶ በመቶ በመክፈላቸውና ቁጥራቸውም ከሚገነቡት ቤቶች በላይ በመሆኑ በዕጣ መለየት የግድ ሆኖአል፡፡

ምንጮቹ አያይዘውም የአስተዳደሩ ጥቂት ሃላፊዎች 40 በ60 ቤቶች መቶ በመቶ ቅድሚያ ለከፈሉ ቅድሚያ ይሰጥ የሚለው ከፕሮግራሙ ዓላማና ለሕዝብ ከተገባው ቃል ተቃራኒ በመሆኑ መተግበር የለበትም የሚል አቋም እንዳላቸው ታውቋል፡፡

በመሃል ከተማ በሰንጋ ተራና ክራውን ሆቴል አካባቢ  ጂ 12 እና ጂ 9 በሚል  የተገነቡት እነዚሁ ቤቶች ከተመዝጋቢው ቁጥር አንጻር ሲታይ  እጅግ አነስተኛና እዚህ ግባ የማይባል መሆኑን የጠቀሱት የአስተዳደሩ ምንጮች፣  የዘንድሮውን አፈጻጸም መነሻ በማድረግ በዓመት 1 ሺ 200 ቤቶች ይገነባሉ ቢባልም፣  164ሺ ቤት ለመገንባት ስንት ኣመት ሊፈጅ እንደሚችል ሲታሰብ ሥራው በመንግስት አቅም ብቻ ሊከናወን እንደማይችል በቂ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይ ሳምንት  እጣ ከሚወጣባቸው ቤቶች ውስጥ  1 ሺህ ቤቶች የ10 በ90 ማለትም ስቱዲዮ ክፍል ያላቸው ሲሆኑ፥ 34 ሺዎቹ ደግሞ የ20 በ 80 ወይንም ኮንዶሚኒየም የሚባሉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ናቸው።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በየካ አባዶ፣ ቦሌ ለሚ፣ ቦሌ ቡልቡላ እና ቱሉ ዲምቱ ሳይቶች እንደሚገኙ ታውቆአል፡፡