የዲፕሎማቲክና የሰርቪስ ፓስፖርት የያዙ ኢትዮጵያዊያን እና የቻይና ዜጎች ብቻ አንዱ ወደ ሌላኛው ሀገር ሲሄድ ያለቪዛ እንዲገቡ የሚያስችል ስምምነት ሰሞኑን ለፓርላማ ቀረበ፡፡

መጋቢት ፬(አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በስምምነቱ መሠረት የዲፕሎማትና ሰርቪስ ፓስፖርት የያዙ የሁለቱ ሀገራት ሰዎች ለ30 ቀናትና እንደአስፈላጊነቱ ሊራዘም የሚችል ቆይታ ያለቪዛ እንዲገቡ ይፈቅዳል፡፡ ይህን ቪዛን የሚያስቀረው ስምምነት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት የሁለቱ ሀገራት ዜጎች ለስራ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እየጨመረ በመምጣቱ ነው ተብሎአል፡፡

በሁለቱ ሀገራት ስምምነት መሰረት ከምክትል ሚኒስትር በላይ የሆነ ማእረግ ያላቸው የማእከላዊ መንግስቱ ባለስልጣናትና ኦፊሰሮች ወይንም ከሜጀር ጄኔራል በላይ የሆነ ማእረግ ያላቸው የመከላከያ ባለስልጣናት ለኦፊሴላዊ ጉብኝት ሲንቀሳቀሱ ያለቪዛ የመግባት መብታቸውን ያስከብራል፡፡

የዲፕሎማቲክ ወይም የሰርቪስ ፓስፖርት የያዙ የዲፕሎማቲክ ሚሲዮን አባላትና ቤተሰቦቻቸው የሌላኛውን ተዋዋይ ወገን ሁሉንም ሕጋዊ ውክልና መስፈርቶች ካሟሉ ፣ ተቀባይ ሀገር  በደረሱ በ30 ቀናት ውስጥ ቪዛ ማግኘት ሳይጠበቅባቸው

እስከ ውክልናቸው ጊዜያቸው መጨረሻ ድረስ ያለቪዛ ወደሀገር መግባትና መውጣት እንደሚችሉ በስምምነቱ ላይ ተቀምጦአል፡፡

ይህ ስምምነት በቻይና ዩኒቨርሲቲዎችና የጦር አካዳሚዎች ውስጥ ከፍተኛ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ የከፍተኛ ባለለስልጣናት ልጆችና ቤተሰቦች እንዲሁም ከከፍተኛ በለስልጣናት ጋር ተቀናጅተው የቻይና ምርቶችን በሚስጢር ለሚነግዱና ለሚያስነግዱ የሥርዓቱ ሰዎች የተሻለ ምቾትን ለመስጠት ታልሞ የተደረገ ስምምነት ሊሆን እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ስምምነቱ ፓርላማው ሰሞኑን ያጸድቀዋል ተብሎ ይገመታል፡፡