መንግስት ሰሞኑን የሚከበረውን የኢድ አልፈጥር በዓል በመግቢያ ካርድ እንዲሆን ያስተላለፈውን መመሪያ በልዩ ትዕዛዝ እንዲቆም ማድረጉን ለኢሳት ከአዲስ አበባ የደረሱ መረጃዎች አመለከቱ

ነሀሴ ፩ ቀን ፩፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-መንግስት በትላንትናው ዕለት የህዝበ ሙስሊሙን የተቃውሞ ስልፍ በመፍራት በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚከበረውን በአል በልዩ የመግቢያ ካርድ እንዲሆን በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የመግቢያ ካርዶችን እንዳዘጋጀ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይሁንና ዛሬ የፌደራል መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ልዩ ትዕዛዝ በመስጠት ሁኔታው እንዲቆም ማድረጉ ታውቋል፡፡

የፌደራል መረጃና ደህንነት ተወካዮች በአዲስ አበባ አስሩም ክፍለ ከተማ የሚገኙ የመጅሊስ አባላትን፣ ካድሬዎችና የደህንነት ሰዎችን በአስቸኳይ በመጥራት ሁኔታው መንግሥትን የሚያዋርድ ነው በማለት በአስቸኳይ እንዲቆም ማድረጋቸውን የኢሳት ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የደህንነት ተወካዮች ሊበተን የተዘጋጀውን ካርድ እንዳይበተን የተበተነም ካለ እንዲሰበሰብ ወይም ጥቅም ላይ እንዳይውል ትዕዛዝ መስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባለፈው ሰኞ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሊካሄድ የታቀደውን የተቃውሞ ስልፍ በመስጋት በአዲስ አበባ የሚገኙ ኢምባሲዎችና የውጭ ሀገር ተቋማት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማስታወቁን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡

የተለያዩ አለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ዋሽንግተን  ፖስትን ጨምሮ በመጪው አርብ ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚካሄድ በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡

ሁለት አመትን ያስቆጠረው የሙሲሊሞች ተቃውሞ ከመቼውም በላይ የአለም አቀፍን ትኩረት በማግኘት ላይ ነው፡፡

አድማጮቻችን ዘግይቶ በደረሰን መረጃ የኢትዮጵያ ፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን   ነገ የሚከበረውን የኢድ አልፈጥር በአል በማስመልከት በአሉ በሰላም እንዲከበር በሚል አስፈላጊ ያለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

ፌዴራል ፓሊስ ባልተለመደ ሁኔታ ባወጣው መግለጫ በክልልና በአዲስ አበባ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ሰላምን የሚያደፈርስ ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ ቢመለከት በአቅራቢያው ለሚገኝ ፓሊስና የጸጥታ አካል አስፈላጊውን ጥቆማ ህዝብ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡

ያልተለመደ የተባለው መግለጫ መንግስት እየተባባሰ በመጣው የሙስሊሞች የተቃውሞ ሰልፍ ውጥረት ውስጥ መግባቱን አመላካች ነው በማለት ብዙዎች አስተያታቸውን በመስጠት ላይ ናቸው፡፡