ከፍተኛው ፍርድ ቤት ባለ አምስት ኮከብ የሆነውን ኢንተርኮንቴነንታል ሆቴል እና ሌሎች ህንጻዎችን ከሙስና ከተጠረጠሩ ባለሀብቶች ተወስደው በገለልተኛ ወገን እንዲተዳደሩ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

ነሀሴ ፩ ቀን ፩፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ፍርድ ቤቱ በትላንትናው እለት የፌደራሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቢ ህግና የተጠርጣሪ ጠበቆች በጋራ ተስማምተው ንብረቱን የሚያስተዳድር አካል እስከ መስከረም 22 ቀን 2006 ዓ.ም. እንዲያቋቁሙ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

ንብረታቸው በገለልተኛ አካል እንዲተዳደር ፍርድ ቤት የወሰነባቸው ንብረትነቱ የአቶ ሰማቸው ከበደ የሆነው ባለ 5 ኮከብ ኢንተርኮንተነንታል ሆቴል እና ዲ ኤች ሲሜክስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እንዲሁም የአቶ ከተማ ከበደ ንብረት የሆነው ኬኬ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ የአቶ ነጋ ገብረእግዚአብሔር ንብረት የሆኑት ነፃ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና ባሰፋ ትሬዲንግ ናቸው፡፡

በሙስና ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የኢንተርኮንተኔታል ባለቤት አቶ ሰማቸው ከበደ በ2004 ዓ.ም. ነበር ሆቴሉን በ320 ሚሊዮን ብር በመገንባት ለስራ ያበቁት፡፡

152 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ሆቴሉ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ዘመናዊ ሆቴሎች አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡

የሆቴሉ ባለቤት በዱባይ ሀገር የአማካሪ ድርጅት እንዳላቸው ሲነገር መንግስት ባለቤቱን በሙስና ክስ በመመርመር ላይ ይገኛል፡፡

የአቶ ከተማ ከበደ ንብረት ደግሞ በቦሌ መንገድ ላይ የሚገኝ ባለ ስድስት ፎቅ ህንፃ ሲሆን በኢትዮጵያ የአለም ባንክ ተወካይ ተከራይቶት በመገልገል ላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በትላንትናው የፍርድ ቤት ውሎ የተከሳሾች ጠበቆች ንብረቶች ይባክናሉ ሠራተኞችም ደመወዝ አልተከፈላቸውም የሚል አቤቱታ ለፍርድ ቤት ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ፀረ ሙስናና የባለሀብቶቹ ጠበቆቻቸው ቅሬታቸውን በማመልከቻ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

በ2012 የወጣ አለም አቀፍ የሙስና ደረጃ ኢትዮጵያ ከ176 ሀገራት በ113ኛ ላይ ትገኛለች፡፡