ሚያዚያ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከሳምንት ሳምንት እየተጠናከረ የመጣው የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ፣ መላው ክርስቲያኖችንን እንዲያካትት ጥሪ እየተላለፈ ባለበት በአሁኑ ወቅት መንግስት ችግሩን በሰላም ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ የሀይል አማራጭን ለመጠቀም ፍላጎት እያሳየ ነው።
የአቶ መለስ ዜናዊን የሰሞኑን የፓርላማ ንግግር ተከትሎ በመላ አገሪቱ የሚገኙ በርካታ ሙስሊሞች ባለፈው አርብ ተቃውሞዓቸውን ካሰሙ በሁዋላ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከመንግስት ጋር በመተባባር ጥያቄውን በሀይል ለመፍታት ፍላጎት አሳይቷል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ከተለያዩ የክልል ኡላማዎች፣ ከዞን እና ከወረዳ ምክር ቤት ሀላፊዎች ጋር በጋራ ተመካክሮ ባሳለፈው አቋም ፣ አክራሪነት መንፈስ የተጠናወታቸው አካላት ህዝበ ሙስሊሙ ሀይማኖቱን ተረጋግቶ እንዳያካሂድ እያደረጉት በመሆኑ ፣ ህብረተሰቡና የጸጥታ አስከባሪዎች ግለሰቦቹን እየያዙ ለህግ ማቅረብ እንዳለባቸው ውሳኔ አሳልፎአል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ አህመዲን ሼህ አብዱላሂ ባለድርሻዎች አክራሪዎችን እየመረጡ ወደ ህግ እንዲያቀርቡዋቸው ጠይቀዋል።
የኢሳት የዜና ምንጮች እንደሚገልጡት ከሆነ በእየሳምንቱ የሚታየው የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ኢህአዴግንና ደጋፊዎችን፣ መንግስትን እና ተከታይ ኡላማዎችን በእጅጉ እያስደነገጠ ነው። የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ሁለት ምርጫዎች አሉት፣ አንድም ሙስሊሙ የሚያቀርበው ጥያቄ የብዙሀኑ ጥያቄ መሆኑን ተረድቶ ለጥያቄው አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት፣ ሌላም ጥያቄው የጥቂቶች ነው በሚል በሀይል ለመጨፍለቅ መሞከር ነው።
አንደኛው አማራጭ እውን ከሆነ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህዝብም ትልቅ ትምህርት ጥሎ ያልፋል የሚሉት ተንታኞች፣ መንግስት በህዝብ ግፊት ጥያቄዎችን መመለስ ከጀመረ ሌሎችም በተመሳሳይ መልኩ ጥያቄያቸውን እየያዙ ለመቅረብ ድፍረቱን ያገኛሉ ይላሉ። መንግስት ጥያቄውን በሰላም ለመመለስ ከፈቀደ ከሁሉም በላይ ተጠቃሚው መንግስት ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ይሆናል፣ ምክንያቱም ህዝብ በጋራ ከተነሳ መንግስትን ማስገደድ እንደሚችል ቱኒዚያ፣ ግብጽ፣ ወይም ሊቢያ ድረስ ሳይጓዝ በራሱ አገር ጥሩ ትምህርት ይቀስማል፣ ቀዳዳውም እየሰፋ ሌሎችም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ለማቅረብ ይደፋፈራሉ ይላሉ።
ተንታኞቹ እንደሚሉት መንግስት ጥያቄውን በሀይል ለመጨፍለቅ ከሞከረም፣ መላው ሙስሊም በጋራ እና በቁጭት እንዲነሳ እንደሚያደርገው እስካሁን የተከተለውን ፍጽም ሰላማዊ ተቃውሞ ወደ ሀይል ተቃውሞ ሊቀይረውና ደም መፋሰስ ሊከተል እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ። ሙስሊሙ ህብረተሰብ በጀመረው ፍጹም ሰላማዊ ትግል መቀጠሉ መንግስት የሚያስደነብረው ይሆናል ሲሉም ያክላሉ።
በሌላ በኩል ግን ሙስሊሙ ያቀረበው ጥያቄ ብሄራዊ አጀንዳ እንዲኖረውና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ ካስፈለገ፣ ሙስሊሙን ከክርስቲያኑ ለማጋጨት በአቶ መለስ መንግስት የተሸረበውን የመከፋፈል ሴራ ማክሸፍ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር መሆኑን አንዳንድ ተንታኞች ይናገራሉ። አቶ መለስ በሰሞኑ የፓርላማ ንግግራቸው ክርስቲያኑ ህዝብ ደንብሮ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ለማድረግ ቢሞክሩም፣ በሙስሊም ሆነ በክርስቲያኑ በኩል ያጋጠማቸው ተቃውሞ እንጅ ድጋፍ አለመሆኑን ተንታኞች ይገልጣሉ። ክርሰቲያኑ ህዝብ አቶ መለስ ገዳማትን ሳይቀር ለማውደም ሲሞክሩ እያየ ለእርሳቸው ቅስቀሳ ጆሮ አይሰጥም የሚሉት ተንታኞች፣ ይሁን እንጅ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄያቸው በዘላቂነት ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ከፈለጉ ክርስቲያኑን ወገን ለማቀፍ ጥረት ማድረግ አለባቸው። የሙስሊሙ ጥያቄ በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው አገራዊ ችግሮች ሲፈቱ በመሆኑ፣ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ለእነዚህ አገራዊ ችግሮች ቅድሚያ በመስጠት መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያሳትፍ መርሀ ግብር ሊነድፉ እንደሚገባ ያሰምሩበታል።
መንግስት በሚወስደው እርምጃ ግራ መጋባቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ሰሞኑን የተወሰኑ ሙስሊሞችን ለማሰር እንቅስቃሴ ቢያደርግም አዝማሚያው ስላስፈራው መልሶ ለቋቸዋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide