የግልገል ጊቤ ቁጥር አንድ የኃይል ማመንጫ ግድብ በደለል ተሞላ

ሚያዚያ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የግልገል ጊቤ ቁጥር አንድ የኃይል ማመንጫ ግድብ በደለል ተሞላ።ችግሩ ፤በአገሪቱ ላይ ከባድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር  እንዳይፈጥር የመንግስት ባለስልጣናት ጭንቀት ውስጥ ናቸው።

አንድ ባለሥልጣን፦”የግልገል ጊቤን ችግር መቅረፍ ካልቻልን፤ይሄ መንግስት ግድብ መገደብ እንጂ፤የገደበውን አይከታተልም የሚል ፖለቲካዊ አንድምታ  ይፈጥርብናል” ሲሉ ተደምጠዋል።

በፓርላማው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፤ ከውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምሕረት ደበበና ከሌሎች ኃላፊዎች ጋር ባለፈው ሐሙስ  በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ሲያካሂዱ እንደገለጹት፣ የግልገል ጊቤ ቁጥር አንድ በደለል የመሞላት ችግር አስቸኳይ መፍትሔ ካላገኘ፤ በአገሪቱ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ላይ ከባድ ተፅዕኖ ማስከተሉ የማይቀር ነው፡፡

‹‹እውነት እንነጋገር፤ እንዲያውም እዚህ ስንወያይ ሚዲያ አንፈልግም [ነበር]፤ ጉዳዮችን በደንብ አይተን መሄድ አለብን፤›› በማለት አስተያየታቸውን መስጠት የጀመሩ አንድ የተወካዮች ምክር ቤት  አባል፤‹‹እንዳየነው ግድቡ ችግር አለበት፤ እዚያው ድረስ ሄደን  ችግሩን እንዳየነው፤በጆንያ አፈር ተሞልቶ ነው  ለመገደብ ጥረት የሚደረገው›› ብለዋል።

 በጉዳዩ ላይ ቀደም ሲልም ከውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር ውይይት የተደረገ ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ ምንም የመጣ ለውጥ እንደሌለ እኚሁ የምክር ቤት አባል ተናግረዋል።

ሌላዋ የፓርላማ አባል በበኩላቸው በቅርቡ ፦‹‹ናይል ዲስኮርስ ፎረም›› በሚል ርዕስ  በተዘጋጀ ወርክሾፕ ላይ ፤ ግልገል ጊቤ ቁጥር አንድ ግድብ -በደለል እየተሞላ መምጣቱን የሚያሳይ ጥናት ያቀረበ አንድ አጥኚ፣ ደለሉ እስከወገቡ ሲውጠው የሚያሳይ ፊልም ለታዳሚው ማቅረቡን ተከትሎ በቦታው የነበሩ ታዳሚዎች ‹‹ ፊልሙ በቴሌቪዥን ይቅረብና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይመልከተው›› የሚል ጥያቄ  ቢያቀርቡም፤ ጉዳዩ በፖለቲካ ረገድ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ከባድ ሊሆን ስለሚችል ተብሎ  ህዝብ እንዳያውቀው መደረጉን ጠቁመዋል።

ደለሉን በጆንያ በተሞላ አፈር ለመከላከል መሞከር ም ፤ችግሩን ከማባባስ ውጪ የሚያመጣው ለውጥ እንደማይኖር አስረድተዋል፡፡

የምክር ቤት አባሏ አክለውም፦‹‹ በጉዳዩ ዙሪያ የቅንጅት ሥራ ሊሠራ ይገባል፤ ነገሩ፤ ለፖለቲካ መጠቀሚያ ሰፊ በር ይከፍታል፤ ሌሎች ወገኖች  ከህዳሴ ግድቦችና ከሌሎች ግድቦች ጋር ያያይዙታል፡፡ ‘ይኼ መንግሥት የሚያውቀው መገደብ ብቻ ነው ወይ? የገደበውን አይከታተልም ወይ?’ የሚል የፖለቲካ አንድምታ የሚያመጣ በመሆኑ፤ ጊዜ ልንሰጠው አይገባም፤›› ሲሉም  ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

ግልገል ጊቡ አንድ እና ሁለት የ ተሠራው በሳሊኒ ኮንስትራክሽን ሲሆን፤ ግልገል ጊቤ ሁለትም በተመረቀ በሳምንታት ውስጥ ለብልሽት ተዳርጎ ለረዥም ጊዜያት ያለ አገልግሎት መቀመጡ ይታወሳል።

ሳሊኒ በግልገል ጊቤ አንድና ሁለት ላይ ሥራዎቹ ላይ የተጠቀሱት ከፍተኛ ጉድለቶች ቢታዩበትም፤  ከ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይፈጃል የተባለውንና በብዙዎች ዘንድ የፖለቲካ ውጥረት ማርገቢያ ተደርጎ የሚወሰደውን የህዳሴውን ግድብ ሥራ፤ ያለ ጨረታ እንዲወስድ መደረጉ ይታወቃል።

ሪፖርተር እንደዘገበው፤በሰሞኑ ውይይት በፓርላማ አባላቱ ከተነሱት በርካታ ችግሮች መካከል  ሌላው፤የግንባታ ጊዜው ያለፈው የ’ርብ’የመስኖ ፕሮጀክት ጉዳይ አንዱ ነው፡፡

የርብ የመስኖ ፕሮጀክትን ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት የጐበኙ መሆናቸውን የጠቆሙ አንድ የቋሚ ኮሚቴ አባል፣ በዲዛይኑ ውስጥ የካናል ሥራ አለመካተቱን፣ ግድቡም አሁን ባለበት ደረጃ ውኃ የመያዝ አቅም የሌለው መሆኑን ከገለጹ በኋላ፣ ‹‹ካናል በሌለበት ሁኔታ ግድቡ እንዴት አድርጐ ለመስኖ እንደሚውል ግልጽ አይደለም፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

“ከዓመታት በፊት የተጀመረው የደምቢዶሎ የውኃ መስመር ዝርጋታ የዘገየበትስ ምክንያት ምንድነው?” የሚል ጥያቄም ከተለያዩ የፓርላማ አባላት ተነስቷል፡፡

ለጥያቄዎቹ መልስ ለመስጠት የሞከሩት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ በበኩላቸው፤ ችግሮች ስለመኖራቸው አምነዋል፡፡

 የደምቢዶሎ የውኃ መስመር ዝርጋታ የተጓተተው በኮንትራክተሩ አልምጥነት መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ በአውሮፓ ኅብረት አበዳሪነት የሚሠራውን ይህንን ፕሮጀክት ከኮንትራክተሩ ጋር ውል በማፍረስ ከማቋረጥ ይልቅ በኮንትራክተሩ ላይ ጫና በማሳረፍ ማሠራት የተሻለ አማራጭ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም፦‹‹ይኼ ገንዘብ የአውሮፓ ኅብረት ገንዘብ ነው፤ ኮንትራክተሩ የመጣው ከአውሮፓ ኅብረት አገሮች ነው፣ አንድ ቦታ ብትቆነጥጥ ሺሕ ነው የምታስጮኸው፤ ኮንትራክተሩን አንነክሰው ነገር ምን እናድርግ?››ሲሉ ግራ መጋባታቸውን ገልጸዋል።

የግልገል ጊቤ ፕሮጀክት ችግር በጣም አስከፊ እንደሆነ  መሥርያ ቤታቸው የተገነዘበው መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

‹‹አንዳንድ ጉዳዮችን አንስቶ የገንዘብ መፈለጊያና መብያ የሚደረግበት ሁኔታ ስላለ ጥናቱን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ነው የምናየው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ የደለል ችግሩን ለመቅረፍ ሁላችንም በአስቸኳይ ልንረባረብ ይገባል ብለዋል።

እንደ ግልገል ጊቤ ዓይነት መለስተኛ ግድቦችን መያዝና ማስተዳደር ከአቅሙ በላይ የሆነበት መንግስት በዓባይ ላይ  ትልቅ ግድብ እሠራለሁ ማለቱ ስህተት እንደሆነ ፤የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ጌታቸው በጋሻው ማስገንዘባቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ አንድ ታላቅ ግድብ ከምትሠራ በርካታ ትናንሽ ግድቦችን ብትሠራ እንደሚመረጥ የመከሩት ዶክተር ጌታቸው፤ ትልቅ ግድብ ከተሠራ በሁዋላ በደለል የመሞላት አደጋ ቢያጋጥም ከውጪ ቴክኖሎጂውን አስገብቶ ለማስጠረግ የሚጠይቀው ወጪ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም።

ግልገል ጊቤ ቁጥር አንድ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን 184 ሜጋ ዋት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። እየተገነባ ነው የተባለው የህዳሴ ግድብ ደግሞ፤ ከ 6 ሺህ በላይ ሜጋ ዋት እንደሚያመነጭ ነው የተነገረው። ይህ ማለት፤ይገነባል የተባለው የህዳሴ ግድብ፤ በማመንጨት አቅሙ አሁን በደለል የተሞላውን ግልገል ጊቤ ቁጥር አንድን፤ ከ 36 ጊዜ በላይ ያጥፈዋል ማለት ነው።

ከዚህ አኳያ “ከስድስትና ከሰባት ዓመት በሁዋላ ይጠናቀቃል የተባለው የህዳሴው ግድብ እንደተባለው ቢያልቅና በደለል የመሞላት አደጋ ቢያጋጥመው፤ ምንድነው የሚኮነው?ምንስ ነው የሚባለው?”ብለዋል-አንድ፤- የግልገል ጊቤ ቁጥር አንድ በደለል መሞላት፤ ለመንግስት ጭንቀት የመፍጠሩን ዜና ያነበቡ አስተያዬት ሰጪ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide