ለትግራይ ተወላጆች የተዘጋጀው ፌስቲቫል ተሰረዘ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 16/2010)

ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በውጭ ለሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በከፍተኛ ወጪ ያዘጋጀው ፌስቲቫል ተሰረዘ።

በመጪው ሃምሌ በመቀሌ ሊካሄድ የነበረው ፌስቲቫል የተሰረዘው በሕወሃት ውስጥ ከተፈጠረው ክፍፍል ጋር በተያያዘ እንደሆነ የቅርብ ምንጮች ገልጸዋል።

ሆኖም ለትግራይ ተወላጆች የተላለፈው መልዕክት ፌስቲቫሉ የተሰረዘው በፕሮግራም መደራረብ ምክንያት ነው የሚል ነው።

በአቶ አባይ ወልዱ የሕወሃት ሊቀመንበርነትና በርሳቸው ቡድን የበላይነት ወቅት የተደረገው ይህ ጥሪ በአይነቱ ልዩና ከፍተኛ ፌስቲቫል እንደሚሆን የተገለጸ ነበር።

በውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በብዛት በፌስቲቫሉ እንዲሳተፉ ከመንግስት ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት እንደነበርም ተመልክቷል።

የአውሮፕላን የደርሶ መልስ ትኬት በቅናሽ እንዲሁም የሆቴል ወጪያቸውን ደግሞ በመንግስት ድጎማ በዝቅተኛ ዋጋ እንደሚይዙ የተገለጸበትና ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገበት ፌስቲቫል የተደናቀፈው በሕወሃት ውስጥ በተፈጠረው ቀውስ እንደሆነም መረዳት ተችሏል።

በአቶ ስብሃት ነጋ የሚደገፈውና ዶክተር ደብረጺዮን የሚመሩት ቡድን ፌስቲቫሉ እንዲቀጥል ጥሪውን ያስተላለፈ ቢሆንም ክፍፍሉ በውጭ በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችም ዘንድ ቅሬታና ስጋትን በማስከተሉ ለፌስቲቫሉ መሰረዝ ምክንያት እንደሆነም ታውቋል።

በዚህም አስቀድመው በፌስቲቫሉ ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳዩና የተመዘገቡ ግለሰቦች ጭምር ወደ ኋላ በማፈግፈጋቸው እንዲሁም ለመመዝገብ ፍላጎት የሚያሳዩት ሰዎች ቁጥርም በመቀነሱ ፌስቲቫሉ ተሰርዟል።

ሆኖም የፌስቲቫሉ መሰረዝ የሚያስከትለው የፖለቲካ መልዕክት ይበልጥ በሕወሃት ደጋፊዎች ዘንድ ብዥታን ይፈጥራል በሚል በፕሮግራም መደራረብ እደነተሰረዘ የሚገልጽ መልዕክት ተላልፏል።

በተለያዩ ማህበራት ለታቀፉ የትግራይ ተወላጆችም በየማህበራቸው አማካኝነት ፌስቲቫሉ ለሚቀጥለው አመት እንደተላለፈም ተነግሯቸዋል።

በዚህ ረገድ በሰሜን አሜሪካ ማለትም በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካና በካናዳ ለሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች “ማህበረ ተጋሩ ሰሜን አሜሪካ” በተባለው ማህበር በኩል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በጥር 22 በተላለፈው መልዕክት በፕሮግራም መደራረብ ፌስቲቫሉ ለ2019 ሐምሌ መተላለፉና የ2018ቱ መሰረዙ ተገልጾላቸዋል።

በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ውስጥ የተፈጠረው ቀውስ አሁንም እልባት ሳያገኝ መቀጠሉ ተሰምቷል።

በአቶ ስብሃት ነጋ የሚመራው ቡድንም በትግራይ ውስጥ የበላይነቱን እያረጋገጠ ቢመጣም በፌደራል ደረጃ ያለው ተጽዕኖና ሚና የተገደበ መሆኑን የውስጥ ምንጮች ይገልጻሉ።

በሕወሃት የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ የሕወሃት መሪዎች ፖለቲካዊና ግላዊ ሚስጥሮች በማህበራዊ ገጽ በመበተን ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

አሁንም እንደቀጠለ መሆኑ ታውቋል።