ነሃሴ ፴(ሠላሳ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስት በሽብርተኝነት በከሰሳቸውና ጉዳያቸው በመታየት ላይ ባለው የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ላይ በፍርድ ቤት ረዥም ቀጠሮ መሰጠቱ አነጋጋሪ ሆነ።
የኢሳት ዘጋቢ ከአዲስ አበባ እንዳጠናቀረው መረጃ ታሳሪዎቹ ብይን ለመስማት ከ3 ወር በላይ መጠበቅ አለባቸው።
በሐምሌ ወር 2004 ኣመተ ምህረት የፈጠራ ሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው ላለፉት ሀለት ኣመታት በእስር ላይ በሚገኙት የሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ የሃይማኖት አባቶችና ጋዜጠኞች ብያኔ ለመስጠት ጉዳያቸውን ሲያስችል የቆየው ፍ/ቤት ለህዳር 23/2006 ቀጠሮ ሰጥቷል።
ለአራት ወራት ያህል በማእካላዊ ወንጀል ምርመራ ሲገረፉና ሲሰቃዩ ቆይተው በህዳር 2005 በአዲሱ የጸረ ሽብር ሕግ ክስ በተመሰረተባቸው በነዚሁ እስረኞች ላይ እሰካሁን ድረስ በከሳሻቸው አሰማኝና በቂ ማስረጃ ሊቀርብባቸው አልቻለም።
ለረዥም ጊዜ በተጓተተው የችሎት ሂደት የአቃቤ ሕግ አሉኝ ያላቸውን ሰነዶችና የሰው ምስክሮች ቢያቀርብም፤ፍርድ ቤቱ በቂ ማስረጃ ሊቀርብ አለመቻሉን እየተመለከተ ብይን ለመስጠት ለህዳር 23/2006 ቀነ ቀጠሮ መ ስጠቱ ቤተሰቦቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ሁሉ ያስቆጣ ሆኗል።
“የብይን ቀጠሮ ለመስጠት እንዲህ የረዘመ ጊዜ መስጠት ለምን እንዳስፈለገ ይገባናል፡፡ በዋነኝነትም ታሳሪዎቹን በጊዜ ርዝመት ጠንካራ መንፈሳቸውን ለማዳከምና በዚያውም ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚሰጥበትን የፍርድ ሂደት ለማመቻቸትና የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ለመስራት ነው፡፡ የፍርድ ሂደቱ ይህ ነው በሚባል ማስረጃ ሳይመረኮዝ ለአስር ወራት ያክል ቢዘልቅም የችሎት ሂደቱ በፖለቲካዊ ውሳኔዎች የተሞላ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን ባለው የችሎት ሂደት ከዚህ በላይ መዝለቅ ባለመቻሉ ችሎቱ ተጨማሪ ጊዜያትን ፖለቲካዊ ውሳኔ ለመስጠት ነው ቀጠሮው የተራዘመው”ብለዋል-ደጋፊዎቻቸው በሰጡት አስተያየት።
ታሳሪዎቹ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ የሃይማኖት ሊቃውንት፣ ጋዜጠኞችና አርቲስቶች በአሰልቺና ከሚዲያና ቤተሰብ እይታ ውጪ እንዲሆን በተደረገው የችሎት ሂደት በጣም በርካታ አሳፋሪ ድርጊቶችን ሲመለከቱና ሲታዘቡ መቆየታቸውም ተነግሯል።
አቃቤ ሕግ በታሳሪዎቹ ላይ 197 ምስክር አለኝ ብሎ ማቅረብ የቻለው 80 ምስክር ብቻ ሲሆን፤ የመንግስት አቃቤ ሕግ የነበረው አቶ ቴዎድሮስ ባህሩ በቅርቡ ከአገር ሸሽቶ አሜሪካ መግባቱ ይታወሳል።