ነሃሴ ፴(ሠላሳ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሰሜን ጎንደር ዞን ነዋሪ የሆኑት ጸጋው አለሙ፤ ዋስይሁን ንጉሱ፤ ጎዳዳው ፈረደ፤ ማማይ ታከለ እና ተገኝ ሲሳይ የተባሉት ሰዎች በኤርትራ ስልጠና ካገኙ በሁዋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ በትግራይ ክልል ማካይዳ ከተማ መያዛቸውን ፋና ዘግቧል።
ተከሳሾች ኤርትራ እና አውሮፓ ከሚገኙ የአሸባሪው ድርጅት የተለያዩ አመራሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር አባላትን እየመለመሉ ወደ ኤርትራ መላካቸውን ገልጾ ፣ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት ተረኛ ችሎት ከጸረ ሽብር ህጉ አንጻር የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ ክሱን ለማሰማት ለጥቅምት 7 2006 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ዜጎች ከአርበኞች ግንባር፣ ከግንቦት 7፣ ኦነግና ኦብነግ ጋር በተያያዘ በቃሊቲና በሌሎችም እስር ቤቶች በመሰቃየት ላይ ይገኛሉ። መንግስት እነዚህን ድርጅቶች በአሸባሪነት መፈረጁ ይታወቃል።