ሚያዚያ ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ ዞን በአና ቦራ ወረዳ በማሊማ በሪ ቀበሌ የሚገኘው የሼር ብሌን ኢትዮጵያ የአበባ እርሻ ባለቤት የሆኑት የሚ/ር ባርኖር ልጅ ሚ/ር ጆን የተባሉት ሆላንዳዊው ባለሀብት በሰራተኞች የተደበደቡት ሚያዚያ 7 ሲሆን፣ ድበደባውን ተከትሎ 27 ሰራተኞች ታስረዋል። ከእነዚህ መካከል 7 ሰዎች ከሶስት ሳምንት በላይ ታስረው በዋስ ሲፈቱ 20ዎቹ አሁንም በእስር ላይ ናቸው።
ከእስር የተለቀቁትና የሰራተኞች ተወካይ የሆኑት አቶ ሚሊዮን ባጫ ለኢሳት እንደገለጹት አሰሪው ባለሀብት ሰራተኞችን እንደ ሰው ልጅ ሳይሆን እንደ አህያ እንደሚሳደብ እና ለሰራተኞች ክብር የሌለው መሆኑን ገልጿል።
በሰውየው ስድቦች የተማረረ አንድ ወጣት ባለሀብቱን መደብደቡን ተከትሎ፣ ባለሀብቱም በመልሱ ልጁን መደብደቡን አቶ ሚሊዮን ገልጸዋል። ሌሎች ሰራተኞች በንዴት ” በሀገራችን ላይ ደማችንን እያፈሰስን እንዴት ይረግጠናል በማለት አሰሪውን መደብደባቸውን አክለዋል
በእስር ላይ የሚገኙት 20 ኢትዮጵያውያን በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከሰው ዋስትና በማጣት በናዝሬት እስር ቤት ታስረው ይገኛሉ።
ሰራተኞች የደሞዝ ፣ የስራ ዋስትና፣ እና ሌሎች አስተዳደራዊ በደሎችን ከማንሳት በተጨማሪ ድርጅቱ የተከለከሉ አንደኛ ደረጃ መድሀኒት መጠቀሙንም ሲቃወሙ መቆየታቸውን አቶ ሚሊዮን ተናግረዋል። ይህንን አደገኛ ኬሚካል በመቃወም ሰራተኞች ተቃውሞ ቢያነሱም የሚሰማቸው እንዳላገኙ አቶ ሚሊዮን ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ባለሀብቱን ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።
በርካታ ኢትዮጵያውያን በቻይና አሰሪዎቻቸው እንደሚማረሩ ቢታወቅም፣ የአውሮፓ አሰሪዎች ስለሚፈጽሟቸው በደሎች ብዙ ሲነገር አይሰማም።