መንግስት ሸቀጦችን የሚያከፋፍል ድርጅት ለማቋቋም እንቅስቃሴውን መቀጠሉ ታወቀ

ሚያዚያ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ ውስጥ በየጊዜው የሚታየውን የሸቀጦች ዋጋ መናር ለማስቀረት ይረዳል የተባለ የንግድ ድርጅት ለማቋቋም በከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኘው መንግስት ፣ ድርጅቱ ከተቋቋመ በሁዋላ የማስተዳደር ስራውን ለአሜሪካው የሸቀጦች አከፋፋይ ድርጅት ለማስረከብ በመነጋገር ላይ መሆኑን ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።

1 ቢሊዮን ብር የመመስረቻ ካፒታል እንደሚመሰረት የተነገረለት የኢትዮጵያ የሸቀጦች ማከፋፈያ ኢንተርፕራይዝ በሚቀጥለው አመት ስራውን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። ድርጅቱ የምግብ ሸቀጦችን በተለይም ዘይትና ስኳር እንደሚያከፋፍል ዘገባው ያመለክታል።

የተለያዩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች የሸቀጦች ዋጋ መናር ዋና ምክንያቱ የአቅርቦት እጥረት ነው በማለት ለኢሳት መናገራቸው ይታወሳል። የኢህአዴግ መንግስት  የችግሩ ፈጣሪዎች  ስግብግብ ነጋዴዎች ናቸው በማለት ስኳርና ዘይትን ሲያከፋፍል ቆይቷል።