ሂውማን ራይትስ ወች በተማሪዎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ አወገዘ

ሚያዚያ ፳፰ (ሃያ ስምንት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ታዋቂው አለማፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚወሰዱት ሃይል የተቀላቀለበት እርምጃ በአስቸኳይ ሊያቆሙ ይገባል ብሎአል።

የመንግስት ባለስልጣናት በእስር ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን መፍታት እንደሚገባቸው ፣ ድርጊቱን የፈጸሙት የጸጥታ ሃይሎችና ባለስልጣናት አስፈላጊው ምርምራ እንዲካሄድባቸው የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ጠይቋል።

የድርጅቱ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሌስሊ ሌፍኮ  የአዲስ አበባን መስፋፋት ተከትሎ በከተማዋ ዙሪያ የሚኖሩ አርሶአደሮች እጣ ፋንታ አሳስቧቸው ተቃውሞ የወጡትን ንጹሃን ዜጎችን ከማጥቃት ይልቅ ፣ መንግስት ከተማሪዎች ጋር ቁጭ ብሎ በመነጋገር መፍትሄ መፈልግ ነበረበት ብለዋል።

ተማበአምቦ፣ ነቀምት፣ ጅማ እና ሌሎችም ከተሞች ተቃውሞ ማድረጋቸውን የገለጸው ሂውማን ራይትስ ወች፣ የጸጥታ ሃይሎች በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ጥይቶችን በመተኮስ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎችን ገድለዋል። መንግስት በአምቦ 8 ሰዎች እንደተገደሉ ቢናገርም፣ የአይን ምስክሮች ግን ቁጥሩ ከዚህ በላይ እንደሚሆን መግለጻቸውን ድርጅቱ  አክሎ ገልጿል።  የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃውን የወሰድኩት ዘረፋ እና ንብረት ማውደም ስለነበረ ነው የሚል ምክንያት መስጠቱንም ድርጀቱ ገልጿል።

መንግስት የነጻውን ፕሬስ እና የሰብአዊ መብት ድርጅቶችን በማዳካሙ በኦሮምያ የደረሰውን ጉዳት በትክክለኛ ለማጣራት አለመቻሉን ፣ ወደ አካባቢው የተጓዙ የውጭ አገር ጋዜጠኞችም በጸጥታ ሃይሎች እንዲመለሱ መደረጉን ድርጀቱ ገልጿል።

ኢትዮጵያ ጋዜጠኖች ከሚታፈኑባቸው አገራት መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኑዋን ሂውማን ራይትስ ወች አስታውሷል።

 መንግስት ሚዲያውንና የሰብአዊ መብት ድርጅቶችን ቢያፍንም ከተጠያቂነት ያመልጣል ማለት አለመሆኑን ምክትል ዳይሬክተሯ ሌስሌይ ሌፍኮው ገልጸዋል።