የቻይናና አፍሪካ ንግድ ወደ 400 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድግ ሊ ኪቺያንግ ተናገሩ

ሚያዚያ ፳፰ (ሃያ ስምንት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የቻይናው ጠ/ሚንስትርሊ ጂያንግ  በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ባደረጉት ንግግር አገራቸው ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ በማሳደግ ከ6 አመታት በሁዋላ የንግድ ግንኙነቱ ወደ 400 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ይላል ብለዋል።

ቻይና ባለፉት አመታት የአፍሪካ ቀዳሚዋ የንግድ ሸሪክ መሆናን ጠ /ሚኒስትሩ ገልጸዋል። አገሪቱ ለተለያዩ አፍሪካ አገራት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር መስጠቷንም ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ጠ/ሚኒስትሩ የአፍሪካ አገራት ዋና ዋና ከተሞችን በባቡር ለማገናኘት አገራቸው የገንዘብ እርዳታ እንደምትለግስ ቢናገሩም ይህ እቅድ መቼ ወደ ተግባር እንደሚሸጋገር የተናገሩት ነገር የለም።

ጠ/ሚኒስትሩ ቻይና ለኢትዮጵያ የባቡር መስመር ዝርጋታ 3 ቢሊዮን ዶላር ብድር እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

ቻይና በአፍሪካ ቁጥር አንድ የንግድ ሸሪክ እየሆነች መምጣቱዋ በአፍሪካ ውስጥ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚደረገውን ግፊት ይቀንሰዋል ተብሎ ይሰጋል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዲፕሎማቲክ ግንኙነታቸውን ከምእራባዊያን አገራት ወደ ቻይና እያዞሩ ነው።