ሁሉን ያቀፈ ሀገራዊ ጉባዔ እንዲጠራ ጥሪ ቀረበ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 23/2010)

በኢትዮጵያ ሁሉን ያቀፈ ሀገራዊ ጉባዔ እንዲጠራ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ማህበር ጥሪ አቀረበ።

ማህበሩ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ የተመለከተ ባለ 34 ገጽ ሪፖርቱን ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ጠመንጃ ያነሱ የነጻነት ሃይሎች፣ በሀገር ቤት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሚመለከታቸው ሁሉም የኢትዮጵያ ድርጅቶች ተሳታፊ የሆኑበት ጉባዔ በመጥራት ኢትዮጵያን ከተደቀነባት ሀገራዊ ቀውስ መታደግ ይገባል ሲል ማህበሩ አስታውቋል።

ሪፖርቱ በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ አፈናዎች፣ ግድያዎችንና መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በዝርዝር ያጋለጠ እንደሆነ ተገልጿል።

የማህበሩ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ሃይለማርያም ለኢሳት እንደገለጹት በኢትዮጵያ የሚፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፉ መጥተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች የፈለጉትን ሀሳብ የማራመድም ሆነ የሚደግፉትን የፖለቲካ ድርጅት በተመለከተ ስሜታቸውን በአደባባይ ለመግለጽ የሚችሉበት እድል ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል የሚሉት አቶ ያሬድ ሁኔታዎች ከምንጊዜውም በላይ እየከፉ መተዋል ይላሉ።

በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ለሰብዓዊ መብት ታጋዮች፣ለጋዜጠኞችና ለሲቪክ ማህበራት ፈጽሞ የሚመች አይደለም ሲሉም ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ማህበር ባወጣው ባለ 34 ገጽ ሪፖርት አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ቀውስ በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የሚያቀርብ ነው።

በኢትዮጵያ አሁን ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን በሪፖርቱ ያመለከተው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ማህበር ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ ከፍተኛ ጥፋት ከማስከተሉ በፊት ሀገራዊ ጉባዔ እንዲጠራ ማህበሩ ጠይቋል።

ሁሉም የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች የሚሳተፉበት ጉባዔ በአስቸኳይ እንዲጠራ በመጠየቅ ለተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች፣ ሃያላን ሀገራትና ለህወሃት አገዛዝ መልዕክት ማስተላለፉን አቶ ያሬድ ለኢሳት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ማህበር በቀድሞ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ውስጥ ይሰሩ በነበሩና በምርጫ 1997 በተፈጠረው ቀውስ ከሀገር በስደት በወጡ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመ ማህበር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።