ጷግሜን ፭፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመጪው መስከረም ወር 2008 መቶ በመቶ በኢህአዴግና አጋሮቹ በተያዘው ፓርላማ ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው
ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ይፋ ለማድረግ በሚል በእነሠራዊት ፍቅሬ እና ሽዋፈራው ደሳለኝ አጋፋሪነት ከምሽቱ 3 ሰዓት ጅምሮ በሚሌኒየም አዳራሽ ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት በሚገኙበት ታላቅ የፌሽታ በዓል ተዘጋጅቷል፡፡
እነሠራዊት ፍቅሬ ከመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ይህ ድግስ ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ፓርላማው ሳይወያይበትና ሳያጸድቀው ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ምንም እንኩዋን ፓርላማውን መቶ በመቶ የተቆጣጠረው ቢሆንም ፣ ለይስሙላ እንኩዋን ሥርዓቱን ጠብቆ ቀርቦ
ሳይጸድቅ ለፕሮፖጋንዳ መጣደፉ ገዥው ፓርቲ ራሱ ላወጣቸው ሕግና ስርዓት እንደማይገዛ አንድ ማሳያ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የመጀመሪያው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ከአምስት ዓመት በፊት በሚሌኒየም አዳራሽ ይፋ ሲደረግ እነሠራዊት ፍቅሬ «ድህነት ደህና ሰንብቺ…. ኩራዥ ወደሙዚየም ይገባል» በሚል ንግግር ሲያሰሙ የነበረ ሲሆን ፣ በዕቅዱ ዓመት መጨረሻ በ2007 ዓ.ም ግን ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያዊያን የተራቡበት፣የኤሌክትሪክ መቆራረጡ
ተብብሶ የቀጠለበት፣ የዋጋ ንረቱም ራሱ መንግስት ባመነው መረጃ መሰረት ወደ 11 ነጥብ 4 በመቶ ያሻቀበበት፣ በገጠርና በከተሞች አካባቢ ሥራ አጥነትና ሴተኛ አዳሪነት የተስፋፋበት፣የመንግስት ሥራ መልካም አስተዳደር የተጓደለበት፣ በየደረጃው ሙስናና ብልሹ አሠራር የተንሰራፋበት ፣ ስደት የተበራከተበት ዓመታት ሆነው ሊጠናቀቅ ግድ ሆኖአል፡፡
በዚህ ዓመት የተጠናቀቀው የመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተለይ በወጭ ንግድ፣ በመሠረተ ልማት እና በኢንዱስትሪ መስክ የታሰበውን ማሳካት ሳይቻል መቅረቱ የሚታወቅ ነው፡፡ በውጭ ንግድ የማምረቻ ዘርፍ የተገኘው 400 ሚሊየን ዶላር ገቢ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ሊሳካ ከሚጠበቀው 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ጋር
ሲነጻጸር አፈጻጸሙ 22 በመቶ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በአገር ደረጃ ከተገኘው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ውስጥ የማምረቻ ዘርፉ የያዘው ድርሻ ከ12 በመቶ የማይበልጥ ሆኖአል፡፡ ይህም የሀገሪቱን የወጭ ንግድ ሚዛን ክፍተት በማጥበብም ሆነ በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ከማከናወን አኳያ፣ ከምንም በላይ ደግሞ ሀገሪቱ
ከውጭ ብድር ለማግኘት እንዳትችል ደካማ አፈጻጸሙ እንቅፋት መሆኑን ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የባቡር መሠረተ ልማት በተመለከተም ተፈላጊው ፋይናንስ በወቅቱ ባለመገኘቱና ከአፈጻጸም አቅም ማነስ ጋር ተያይዞ የአዲስአበባን ቀላል ባቡር ጨምሮ ሌሎችንም ማሳካት ሳይቻል ቀርቶአል፡፡
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ግብርና መር ፖሊሲ እከተላለሁ የሚለውን በመርሳት በመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዱ ከግብርና ወደኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ሽግግር አደርጋለሁ ቢልም በተለይ የግሉን ዘርፍ በተገቢው ሁኔታ ባለማሳተፉ ሊሳካ አልቻለም፡፡
ሁለተኛው ዕቅድም እነዚህ ችግሮች ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ በሚገባ ባልተገመገሙበት ሁኔታ ወደተግባር የሚገባ በመሆኑ የመሳካቱ ነገር አጠራጣሪ መሆኑን ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።