አዲሱ የኢህአዴግ ሊ/መንበርና የወደፊቱ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ፤ ትናነት ወደሶማሊያ ማቅናታቸው ታወቀ። አቶ ሀይለማሪያም በኢህአዴግ ሊ/መንበርንት ከተመረጡ የመጀመሪያቸው በሆነው የውጭ አገር ጉብኝታቸው ወደሞቃዲሾ ያመሩት፤ በአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት በዓለ-ሲመት ላይ ለመገኘት መሆኑ ታውቋል።
የሶማሊያ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት፤ ባለፈው ጳሁሜ 5 ቀን ሀሰን ሼክ መሀመድን ፕሬዚዳንት አድርጎ መምረጡ የሚታወቅ ሲሆን፤ በአዲሱ ፕሬዚዳንት ቃለመሀላ ስነስርት ላይ አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ፤ ሌሎች የጎረቤት አገሮች መንገስታትና የተባበሩት መንግስታት ተወካዮች ተገኝተዋል።
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ሼክ ሸሪፍ አህመድን ካሸነፉ በሁዋላ ባለፈው ረቡእ ከግድያ ሙከራ እንዳመለጡ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ሰራዊት እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከ1998 ጀምሮ በሶማሊያ እንደሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን፤ አያሌ የሶማሊያ ተወላጆች የኢትዮጵያ መንግስት በሶማሊያ ጉዳይ ጣልቃ ይገባል ብለው ይከሳሉ።
የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ከተቋቋመ እንደአውሮፓ አቆጣጠር ካለፈው 2004 አ.ም ወዲህ፤ እንዲሁም በሶማሊ ታሪክ ከ40 አመት በሁዋላ፤ ሀሰን ሼክ መሀመድ መደበኛ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ተደርገው የተመረጡ ሲሆን፤ በትናንትናው እለት አገሪቱን በፕሬዚደንትነት ለማገልገል ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።