በኢትዮጵያ ግጭቶችን በመቀስቀስና ዜጎችን በማፈናቀል 1ሺህ 300 የሚሆኑ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 1/2011) የኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችን በመቀስቀስና ዜጎችን በማፈናቀል ከተጠረጠሩ 2500 ሰዎች 1ሺህ 300 የሚሆኑት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ክፍል ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለኢሳት እንደገለጹት ከእነዚህ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሶቦች የክልል አመራሮች ይገኙበታል።

መንግስት በርካታ ግጭቶችን ከመከሰታቸው አስቀድሞ ማምከን መቻሉን የገለጹት አቶ ንጉሱ ቢከሰቱ ኖሮ ለአያሌ ዜጎች ሞት መንስዔ ይሆኑ ነበር ብለዋል።

ግጭቶችን በማባባስ ሚዲያዎች አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም አቶ ንጉሱ ገለጸዋል።

መንግስት ባደረገው ጥናት የግጭቶቹና የመፈናቀሉ መንስዔ ከሆኑት መካከል ማንነትና የወሰን ጉዳይ በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው ሲሉ አቶ ንጉሱ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።