የአፋር ሶስት ቀበሌዎች ይመለሱ ሲል ያሳለፈው ውሳኔ አግባብነት እንደሌለው ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 1/2011) የሶማሌ ክልል ምክር ቤት የአፋር ሶስት ቀበሌዎች ይመለሱ ሲል ያሳለፈው ውሳኔ አግባብነት የሌለው ነው ሲል የአፋር ህዝብ ፓርቲ አስታወቀ።

የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ኮንቴ ሙሳ ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ከሆነ ከሶማሌ ክልል ተወስደዋል የተባሉት ቀበሌዎች ድንበር ላይ ያሉ ሳይሆኑ 300 ኪሎ ሜትር ወደ አፋር ክልል የገቡ ናቸው።

ይህ ባለበት ሁኔታ አይነቱን ጥያቄ ማንሳት አግባብነት የሌለውና የህዝብን መብት የሚገፍ ነው ብለዋል።

ቀበሌዎቹ ምናልባትም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸው መሆናቸውና ያ ጥቅማቸው የተነካባቸው ሰዎች የቀሰቀሱት ሊሆን ይችላሉም ብለዋል።

የአፋር አርብቶ አደር ሳይገደል ያደረበት ቀን የለም ያሉት ዶክተር ኮንቴ እንዲህ አይነቱ ኢሰብአዊ ድርጊት ሊቆም ይገባዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ዶክተር ኮንቴ እንደሚሉት ከሆነ ዋናው ነገር የአካባቢው ሰላም ተጠብቆ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ሁሉም ወገኖች ችግሩን በሰላም ለመፍታት መጣር አለባቸው ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አማካሪ አቶ ጀማል ደርዬ በበኩላቸው እነዚህ ቀበሌዎች ያለህዝብ ይሁንታ ወደ አፋር ክልል እንዲካለሉ ተደርገዋል ነው ያሉት።

ይሄ ውሳኔ ደግሞ የህዝብ ቁጣን ቀስቅሷል በዚህም ምክንያት የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ወደዚህ ውሳኔ ተሸጋግሯል ብለዋል።

አሁን ላይ ግን በሁለቱ ክልሎች መካከል ችግሮች መፈጠራቸውንና እነዛን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው ብለዋል።