የአኝዋክ ተወላጅ የሆነ ወጣት በመከላከያ ሰራዊት ተገደለ

ሚያዚያ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ድርጊቱ የተፈጸመው ያለፈው ቅዳሜ ሲሆን ወጣቱ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በአንድ ባህላዊ ስነስርአት ላይ ተገኝቶ ስነስርአቱን በመካፈል ላይ ነበር። የጋምቤላን የጸጥታ ማስከበር ስራ ከክልሉ መንግስት የተረከቡት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወጣቱን በቅርቡ 19 ሰዎች ከተገደሉበት ድርጊት  ጋር እንደሚጠረጥሩት እና ለጥየቃ እንደሚፈልጉት በመግለጥ አብሮአቸው እንዲሄድ ያዙታል፤ በሁኔታው ግራ የተጋባው ወጣትም ከእነርሱ ጋር አብሮአቸው እንደማይሄድ ሲገልጥላቸው አንደኛው ወታደር ሽጉጥ አውጥቶ ገድሎታል ብሎአል ዘጋቢያችን።

በአካባቢው የነበሩ ወጣቶች በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ድንጋይ በመወርወር እርምጃውን ተቃውመዋል፡፡ የመከላከያ ሰራዊት አባላቱም ማምሻውን ወደ  ሆቴሎች በመግባት በመዝናናት ላይ የነበሩ ወጣቶችን እየደበደቡ ወደ እስር ቤት ወስደዋቸዋል። በማግስቱ እንዲሁም ዛሬ የወታደሮችን እርምጃ ለመቃወም ነዋሪዎች ቤታቸው መቀመጣቸውን ዘጋቢያችን አክሎ ገልጧል።

መከላከያ የጸጥታ ማስከበሩን ስራ ከተረከበ በሁዋላ በነዋሪዎች ላይ የሚፈጸመው  የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መጨመሩን የገለጠው ዘጋቢያችን ሰዎች መንገድ ላይ እየቆሙ ይፈተሻሉ፣ ይደበደባሉ፣ ወደ እስር ቤቶችም ይጋዛሉ ብሎአል።

የሰራዊቱ አባላት ከደቡብ ሱዳን እየፈለሱ ወደ ጋምቤላ በሚገቡት ላይም እንዲሁ ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸሙ ነው። ጫካዎችን በሙሉ የተቆጣጠሩት የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ነዋሪዎች ለእንጨት ለቀማ ወደ ጫካዎች ሲያመሩ እየያዙ እንደሚገርፉዋቸው ገልጧል።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ሚዚያ አንድ 2004 ዓም ባወጣው ዘገባ እንደገለጠው ደግሞ የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው የ18 አመት ወጣት ቲዶ ኩል ኡማን የቀብር ስነስርአት በሚፈጸምበት ወቅት ሽማግሌዎቹ ” የጉዳታችንን መጠን እናውቀዋለን።የሀዘናችንንም ጥልቀት እናስተውላለን። በመሬታችሁ ላይ ሙቱ፣በመሬታችን ላይ እንሙት፣ ሁላችንም እናልቃለን እንጅ መሬታችንን ለቀን ወዴትም አንሄድም። አትፍሩ፣ መንፈሰ ጠንካራ ሁኑ፣ የበቀል መልክተኛ አትሁኑ፣ ለፍትህ ግን ቁሙ። ረዳት እንደሌለን አንሁን ፣ ልጃችን ግን እረፍት ላይ ነው” ብለው መናገራቸውን ዘግቧል።

የአካባቢው ወጣቶች ወጣት ቲዶ ኩልን ጠቁሞ አስገድሎታል ብለው የጠረጠሩትን አንድ ነጋዴ ቤት ማቃጠላቸውን ንቅናቄው ዘግቧል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሟቹን አስከሬን ለመውሰድ ሲመጡ አኛች የተባለው የሟች የክፍል ጓደኛ ጃኬቱን አውልቆ አስከሬኑን በመሸፈን ” እኔንም ግደሉኝ ፣ ሁላችንምም  ግደሉን ፣ ወንድሜን አትወስዱትም” በማለት ሲናገር አብረውት የነበሩትም ተቃውሞአቸውን አሰሙ፤ ወታደሮችም በወጣቶች ላይ ድብደባ ፈጸሙ ።

ንቅናቄው እንዳለው ” የሟች አባት የሆኑት ኩል ኡማን የዲግ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ በመሆናቸው የልጃቸውን ሞት ከሰሙ የበቀል እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ በመፈራቱ ትጥቃቸውን እንዲፈቱና እንዲታሰሩ ተድረጓል።”

ባለፈው ሀሙስ ደግሞ አቦቦ ወረዳ አኩና ቀበሌ አንዲት ሴት ውሀ ቀድታ ስትመለስ ባልሽ የት ነው ተብላ በወታደሮች ስትጠየቅ ” አላውቅም” በማለት በመመለሷ በዱላ እንደደበደቡዋት በመጨረሻም በፍም እንደጠበሱዋት ፣ ሴቲቱም ክፉኛ በመጎዳቷ በአበቦ ሆስፒታል እንደምትገኝ ታውቋል።

ትምህርት በማቆሙ ምክንያት ሻንጣውን ይዞ ወደ ጋምቤላ ሲያመራ የነበረ መምህርም እንዲሁ እንደ አውሬ በመንገድ ላይ በወታደሮች ተገድሏል። አንድ የንዌር ተወላጅ የሆነ መምህርም እንዲሁ መገደሉን ንቅናቄው ገልጧል።

ዘጋቢያችን እንደገለጠው ደግሞ መምህራን ላለፉት 2 ወራት ሳይከፈላቸው የቆየው ደሞዛቸው ተከፍሎአቸዋል፤ ይሁን እንጅ ሌሎች ቃል የተገቡላቸው ጥቅማ ጥቅሞች ባለመከበራቸው አሁንም ትምህርት አንጀምርም በማለት አድማ ላይ ናቸው። በርካታ ተማሪዎቹን በቅርቡ በተፈጸመ ግድያ ያጣው የጋምቤላ ኮሌጅም ከአጎራባች ከተሞች የሚመጡ ተማሪዎች ለህይወታችን ዋስትና ሳይሰጠን አንማርም በማለታቸው አሁንም እንደተዘጋ ነው።

በጋምቤላ አለው ውጥረት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እንጅ እየቀነሰ አለመሄዱን ዘጋቢአችን አክሎ ገልጧል። የመለስ መንግስትም ጋምቤላ በወታደር እንድትመራ  በማድረጉ ችግሩ እየተባባሰ በመሄድ ላይ ነው።

_________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide