በአርማጭሆ የካርቱም አስተዳዳሪ ጥቃት ተፈጸመባቸው

ሚያዚያ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከአማራ ክልል ተቆርሶ ለሱዳን የተሰጠውን መሬት ለማስመለስ ወደ አርማጭሆ የተጓዙት የካርቱም አስተዳዳሪ ጥቃት ተፈጸመባቸው

አተያር የተባለው የሱዳን ጋዜጣ እንደዘገበው የካርቱም አስተዳዳሪ የሆኑት  ከረመላ አባ ሼክ ከትናንት በስቲያ የመለስ መንግስት የለገሳቸውን መሬት በጉልበት ከአርማጭሆ ህዝብ አስመልሳለሁ በማለት ወደ አማራ ክልል እየተጓዙ ነበር። አስተዳዳሪው ወደ ቦታው ደርሰው ገበሬዎቹን ሰብስበው በማነጋገር ላይ እያሉ፣ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ 5 የአስተዳዳሪው ጠባቂዎች ሲቆስሉ አስተዳዳሪው አምልጠው ካርቱም ገብተዋል።

ትናንት ካርቱም ገብተውም ” ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ግንኙነት ከዛሬ ጀምሮ ተቋርጧል” የሚል መግለጫ ሰጥተዋል።

ከ5 አመታት በፊት የመለስ መንግስት ለሱዳን የሰጠውን መሬት የአርማጭሆ ህዝብ  አናስረክብም ብሎ እያረሰ እንደሚገኝ ይታወቃል። አስተዳዳሪውም ይህን መሬት ከህዝቡ ጋር በመወያየት ለማስመለስ እቅድ እንደነበራቸው ታውቋል።

ኢሳት ያነጋገራቸው በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ጥቃቱን የፈጸሙትን ሰዎች የሚያውቋቸው ቢሆኑም ለደህንነታቸው ሲባል እንደማይገልጡ ተናግረዋል። ይሁን እንጅ ታጣቂዎቹ የአገራቸው መደፈር የሚያስቆጫቸው ሀይሎች መሆናቸው ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሁለቱም ሱዳኖች ሱዳን ፓውንድ ከዶላር ጋር ሲነጻጸር በከፍተና ደረጃ በመውደቁ፣ በአካባቢው ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ስራ ለሚሰሩ የህወሀት ኩብንያዎችና ሸሪኮች ከፍተና ኪሳራ ሊያመጣ እንደሚችል ታውቋል።

በደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የቢዝነስ ስራ የሚሰሩት የህወሀት ኩባንያዎችና ሸሪኮች ሲሆኑ፣ የፓውንድ ዋጋ  በፍጥነት ማሽቆልቆል ለባለሀብቶቹ ትልቅ ስጋት ፈጥሯል።

_________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide