በጥቁር አንበሳ የህክምና ዶክተሮች ባለባቸዉ መሰረታዊ የኑሮ ጫና ምክንያት የስራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉ አስጠነቀቁ : ጥያቄያቸዉ እስከ ጥቅምት 15/2004 መልስ እንዲሰጠዉ የጊዜ ገደብ ሰጥተዋል

ኢሳት ዜና:- ከ400 በላይ የሚሆኑት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በማስተማርና የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የህክምና ዶክተሮች በአገሪቱ ያለዉ የኑሮ ዉድነትና የመኖሪያ ቤት ችግር በህይወታቸዉ ላይ ከፍተኛ ድቀት እያደረሰባቸዉ በመሆኑ መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጣቸዉ ጠይቀዋል።

አዲስ ነገር የመረጃ መረብ አዲስ አድማስ ጋዜጣን በመጥቀስ እንደገለፀዉ የህክምና ባለሙያዎቹ በጥቁር አንበሳ ግቢ ውስጥ ባደረጉት ስብሳባ ጥያቄያቸዉ የፖለቲካ ወይም የዐመፅ ሳይሆን ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ በመሄድ ላይ ካለዉ የኑሮ ውድነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገልፀዋል።

የሕክምና ዶክተሮቹ በስብሰባቸዉ መጨረሻ ባለ ሦስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አዉጥተዋል።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሐኪም በሙሉ የሚኖረው ባላሰበው የስቃይ ሕይወት ውስጥ ነው። በዚህ ሁኔታ ሕይወቱን እየመራ ካለው ሐኪም ሞያዊ ሥነ ምግባሩን የጠበቀ ሥራ እንዲሠራ መጠበቁ የዋህነት ነው።

ችግራችን ሕብረተሰቡን ላለማገልገል የቀረበ የፖለቲካ ወይም የዐመፅ ጥያቄ አይደለም። ችግራችን መሠረታዊ የሕልውናና እና የመኖር ጥያቄ ነው።” ብለዋል ጥያቄያችን እስከ ጥቅምት 15 ቀን ድረስ ምላሽ ካላገኘ ሥራ እና ትምህርት ለማቆም እንገደዳለን ያሉት የህክምና ባለሙያዎች በጥቁር አንበሳ ግቢ ውስጥ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ይሰጣችሁዋል የተባለው ሕንጻ ለውጭ ዜጎች እንደሚሰጥና በምትኩ እነሱ በህንፃዉ ምድር ቤት ውስጥ ያሉትን 14 ጠባብ ክፍሎች እንዲወስዱ መወሰኑ እንዳስከፋቸዉ ጠቅሰዋል።

“በቂ የሆነ የመጸዳጃ ቤት እንኳ የሌላቸውን ጠባብ ክፍሎች ለመስጠት መታሰቡ እና ለእኛ እየተዘጋጀ የነበረውን ሕንጻ ለውጭ ዜጎች መስጠቱ በአፓርታይድ ይታይ ከነበረው የነጮች የበላይት እንደማይለይ እና በግቢውም ውስጥ ይህ ዐይነቱ አሠራር መስፈኑን ተረድተናል” በማለት ባለሙያዎቹ ምሬታቸዉን ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ትምህርት ኮሌጅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር አታላይ ዓለም “ችግሩ የሚታይ እና ግልጽ ቢሆንም መፍትሔ ማግኘት ከኮሌጁ አቅም በላይ ነው” በማለት መግለፃቸዉን የመረጃ ምንጮቹ ጠቅሰዋል።

በአገሪቱ በአማካይ የኑሮ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ በሚታሰቡት የህክምና ባለሙያዎች ላይ ትልቅ ጫና የፈጠረዉ የኑሮ ዉድነት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘዉን ድሃ የህብረተሰብ ክፍል ምን ያህል እየገደለዉ እንደሆን አመላካች ነዉ።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊያን የህክምና ባለሙያዎች ያስተማራቸዉን ድሃ ህዝብ ከማገልገል ይልቅ በተገኘዉ አጋጣሚ ወደ ባዕድ አገራት እንዲኮበልሉ የሚገደዱት በኑሮና በፖለቲካ በሚደርስባቸዉ ምሬት እንደሆነ በመደጋገም የሚገለፅ አሳሳቢ ችግር መሆኑ ይታወቃል።