በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የሰፈነው የመልካም አስተዳደር እጦት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አመጽን ሊቀሰቅስ እንደሚችል የፌዴራል ጉዳዮች ሚንስትር መሥሪያ ቤት ያስጠናው አንድ ጥናት አመለከተ።

ኢሳት ዜና:- ጥናቱ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሚታየው የመልካም አስተዳደር እጦት ህብረተሰቡን ወደ አመጽ መንገድ እየመራው መሆኑን አመልክቷል።
የሙያተኞች ግብረ ኃይል የሕዝብ አደረጃጀትና የደህንነት ጉዳይ በሚል ርእስ ባጠናው ጥናት ሁልቆ መሳፍርት ችግሮችን ዘርዝሯል።

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በምክትል ከንቲባዎች የሚመሩ ከህብረተሰቡ የተውጣጡ የአማካሪዎች ምክር ቤት እንዲቋቋም እና የግምገማና የክትትል ሥራ እንዲሰራ የሚል የመፍትሄ ሀሳብ በጥናቱ ውስጥ ቀርቧል።

ከመፍትሄዎች አንዱ ከነዋሪዎች፣ ከምሑራን፣ ነጋዴዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና ባለሃብቶች የሚሳተፉበት የአማካሪዎች ምክር ቤት በከንቲባ ፣ በዞን፣ በወረዳና በቀበሌዎች ጽ/ቤቶች ደረጃ እንዲቋቋም የሚል ነው።

ይሄን አይነት አሠራር የአዲስ አበባ መሥተዳደር በከንቲባ ብርሃነ ደሬሳ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገው ሲሆን፣ በአንፃራዊነት ጥቅም በማስገኘቱ የድሬዳዋ መሥተዳደርም ተሞክሮውን ወስዶ አመርቂም ባይሆንም ለውጥ እንዳመጣበት ያትታል።

ይህ የአማካሪዎች ምክር ቤት አባላት ከህብረተሰቡ ልዩ ልዩ ክፍሎች የሚወከል ሲሆን ፤ የመንግሥትን አሠራር በትክክል መፈጸሙን የሚገመግም፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትንና ሹማምንቶችን ትክክለኛ ድርጊት የሚከታተል፣ ህብረተሰቡን የሚያደምጥ፣ የመንግሥት ኃላፊዎች ሪፖርቶችን ትክክለኛነት እየተቆጣጠረና እየተከታተለ ኃላፊነት ያለባቸውን ሰዎች ተጠያቂ እንደሚያደርግ ይናገራል።

ፌደራል መንግስቱ በሁለቱ ክልሎች ህዝባዊ አመጽ ሊነሳ ይችላል የሚለው ጥናት ከቀረበ በሁዋላ በኦህዴድና በብአዴን ላይ ሰፊና እስከ ወረዳ የዘለቀ ግምገማ እንዲካሄድ አዟል።
በዚህም የተነሳ ለረጅም ጊዜ የብአዴን አባላት ሆነው ያገለገሉ ነባር ተጋዮች የመጀመሪያ ዲግሪ ባላቸው ወጣቶች እንዲተኩ እየተደረገ ነው።

ኢሳት በአማራ ክልል የሚካሄደው ግምገማ እስከ ነፍስ መጠፋፋት ማድረሱን መዘገቡ ይታወሳል።
በተመሳሳይ ዜና የብአዴኑ አቶ ከፍያለው አዘዘ ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባነታቸው፤ አቶ ሉልሰገድ ይፍሩ ደግሞ ከአዲስ አበባ ኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ሀላፊነታቸው ተሻሩ።
ለረዥም ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሆነው የቆዩት የብአዴኑ አቶ ከፍያለው ወደ አዲስ አበባ መስተዳድር ምክትል ከንቲባነት የተዛወሩት፤ በከንቲባ ኩማ ደመቅሳ የሚመራው ካቢኔ የአዲስ አበባን መስተዳድር ሲረከብ ነው።

ከአዲስ አበባ የሚወጡ ዜናዎች እንደሚያመለክቱት፤ ሰሞኑን ኢህአዴግ እያደረገ ባለው የከፍተኛ ደረጃ ግምገማ፤ በርካታ ሹመኞች እየተባረሩ ነው።
በግምገማ ከኃላፊነታቸው ከተነሱት ከፍተኛ የአመራር አባላት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ከፍያለው አዘዘ፣ የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ልዑል ሰገድ ይፍሩ እና የአራዳ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈፃሚ ይገኙበታል ።

ከኃላፊነታቸው የተነሱት የኢህአዴግ አመራር አባላት፤ “ተከሰተ” ለተባለው ሁኔታ ተጠያቂ የተደረጉ፣ አሁን ፓርቲው እየወሰደው ባለው የእሳት ማጥፋት እንቅስቃሴ ውስጥ ትጋት ያልታየባቸውና መመሪያውን ተግባራዊ ያደርጋሉ ተብሎ ያልታመነባቸው ናቸው ተብሏል።

ኢህአዴግ በቅርቡ ባደረገው የከፍተኛ አመራር ግምገማ ላይ፤ በአዲስ አበባ “የ1997 ዓ.ም ዓይነት ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ” በማለት የዳሰሳ ምልከታ ያቀረበ ሲሆን፤ በመጪው ዓመት ለሚካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ በትጋት ለመሥራትና ድባቡን ለመቀየር ከዲፕሎማ በላይ በመማር ላይ የሚገኙ አባላቱ ትምህርታቸውን አቋርጠው ከወዲሁ ለምርጫው እንዲሰሩ ማዘዙ ይታወሳል።