ከነገ እኩለ ሌሊት እስከ ኦገስት 19 ወይም ነሐሴ 13 በዋይት ሀውስ ፊት ለፊት የሚደረገው የረሀብ አድማ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን የመብት ረገጣ አጉልቶ ለማሳየት እንደሚረዳ የረሀብ አድማው አዘጋጅ ቃል አቀባይ ለኢሳት ገለጹ::
ቃል አቀባይዋ ወይዘሪት ትርሲት ጌታቸው፤ ነጻ ሚዲያ ለኢትዮጵያ የሚባለው ቡድን የረሀብ አድማ እንዲደረግ የወሰነው በሀገራችን እየተባባሰ ያለውን የመብት ገፈፋ በተለይ ደግም በጋዜጠኞች ላይ የተጣለውን አፈና እስርና እንግልት በመቃወም መሆኑን ገልጠዋል::
ወ/ት ትርሲት አክለውም የፕሬዝደንት ኦባማ አስተዳደርም ለዚህ አሳሳቢ ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥና ለኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ መልሶ እንዲያጤን የረሀብ አድማ አድራጊዎቹ እንደሚያሳስቡ አስረድተዋል።
በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በላፋይት እስኩዌር የሚደረገውን ይህንን የረሀብ አድማ እንዲያበረታቱና እንዲደግፉ ቃል አቀባይዋ ጥሪ አቅርበዋል::