የአቡነ ጳውሎስ ቀብር ነሀሴ 17 ቀን እንደሚካሄድ ታውቋል

(Aug. 17) በትናንትናው እለት ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ ቀብር በመጪው ሀሙስ ነሀሴ 17 ቀን እንደሚካሄድ ተነገረ።
ከስፍራው ባገኘነው መረጃ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ከየአገረስብከቶቻቸው ወደአዲስ አበባ እየገቡ እንደሆነም ታውቋል።
በኢትዮጵያ የሚገኘው የአገር ቤቱ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ እንደተቀመጠ የታወቀ ሲሆን፤ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ስራአስኪያጅ የሆኑት፤ ብጹእ አቡነ ፊልጶስ በጊዜያዊነት የሲኖዶሱ ሰብሳቢ እንደሆኑ ታውቋል።
በትናንትናው እለት አራት ሊቃነ ጳጳሳት በደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ተገኝተው በድንገት የሞቱትን ፓትሪያርኩን አስከሬን ቢገንዙም፤ የፓትሪያርኩ አሟሟት አጠራጣሪ ነው በሚል ምክንያት ግንዘቱ ተፈቶ፤ ተጨማሪ የአስከሬን ምርመራ እንደተካሄደ ደጀ ሰላም የተሰኘው ድረገጽ ዘግቧል።
ወደአቡነ ገሪማ ደውለን በስልክ አናግረናቸው በፓትርያርኩ ሞት የተሰማቸውን አዘን ገልጸውልን፤ ተጨማሪ አስተያየት ለመስጠት ግን ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
የአቡነ ጳውሎስ አስከሬን በመጪው ሀሙስ፤ በብጹእ አቡነ ተክለሀይማኖት መቃብር ጎን እንደሚያርፍ ለማወቅ ተችሏል።