(Aug. 15) የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለን በ3 የተለያዩ ክሶች ተከሶ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረበ።
ተመስገን ደሳለኝ የክስ መጥሪያ ሳይደርሰው መከሰሱን የሰማው በሬድዮ መሆኑን ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ የገለጸ ሲሆን፤ ይህም የደርግ ግዜውን አፈሳና እስራት አስታውሶኛል ብሏል።
በከፍተኛው ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ የቀረበው የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ “ችሎት አልተሟላም ተብሎ” ክሱ ሀሙስ ነሃሴ 17 ቀን እንዲታይ ቀጠሮ ተሰጥቶት መሰናበቱን አስታውቋል።
ከአመት በፊት በጻፋቸው ጽሁፎች መከሰሱን የገለጸው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ “ወጣቱን ለአመጽ ማነሳሳትና የሀገር ገጽታ በማበላሸት” የሚሉት ክሶች ከክሱ ውስጥ መካተታቸውን ገልጿል።
መከሰሴን ያረዳኝ የሬድዮ ፋና መልእክት “የተመሰረተብህ ክስ አደገኛ ነው፤ ከሀገር ውጣ” የሚል መልእክት አለው ያለው ተመስገን ደሳለኝ፤ ቢሮ ድረስ መጥተው ከሀገር እንደወጣ የመከሩኝን ወዳጆቼን አመሰግናለሁ። ግና ከሀገሬ ሌላ፤ ሌላ አገር የለኝምና የትም አልሄድም ሲል ተናግሯል።
ፍትህ በቅድሚያ እንዳይሰራጭ የታገደው፤ በጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የጤና ሁኔታና በሙስሊሞች እንቅስቃሴ ዙሪያ ዘገባ በመያዝ ሳቢያ ሲሆን፤ ከዚያ በሁዋላ እንዳይታተም፤ ማእቀብ እንደተጣለበት ይታወሳል።