በአዋሳ ጨምበላላ በዓል ላይ ሕዝቡ ተቃውሞውን አሰማ

(Aug. 15) በአዋሳ ከተማ፤ ፊቼ ጫምባላላ በመባል የሚታወቀውን የሲዳማ ብሄረሰብ አዲስ አመት ለማክበር የወጡ፤ ከአምስ መቶ ሺ የሚልቁ ኢትዮጵያዊያን መንግስትን የተቃወመ ትእይንት አደረጉ።
በትላንትናው እለት በተጀመረው በዚህ በአል ላይ ህዝቡ ከዚህ ቀደም የተነሳውን የሲዳማ ዞን የክልል ጥያቄ ዳግም አስተጋብቷል። ኢህአዴግንና የክልሉን ፕሬዝዳንት አቶ ችፈራው ሽጉጤንም በጽኑ አውግዟል።
ህዝቡ በጭፈራው መሀል ፍትህና ነጸነት በመጠየቅ፤ ይህን የነፈገውን የኢህአዴግ መንግስት፤ “ኢህአዴግ ሰለቸን፤ በቃችሁን፤” በማለት በተደጋጋሚ ድምጹን ማሰማቱን ምንጮቻችን ከአዋሳ ዘግበዋል።
ኢሳት ያናገረው አንድ ነዋሪ እንደገለጸው ከሆነ፤ በቦታው የነበሩ ያልተመጣጠነ ሀይል ያላቸው የፌደራል ፖሊስ አባላት የህዝቡን ጥያቄ ለማስቆም ያደረጉት ሙከራ ኢምንት እንደነበር፤ ይህም መንግስት አለመረጋጋቱንና መዳከሙን የሚያመለክት መሆኑን ያሳያል ብሏል።